AMN- መስከረም 10/2017 ዓ.ም
የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አመራሮች ከቤጂንግ የንግድ ሙኒሲፓል ቢሮ የውጭ ኢኮኖሚና የንግድ ዘርፍ ዳይሬክተር ዡዋንግ ጂያንሮንግ ከተመራ የንግድ ልዑካን ቡድን ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይታቸውም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል።
የኢንቨስትመንት ኮሚሽኑ ተወካዮች ለልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ማዕቀፎች ገለጻ ማድረጋቸው ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ለቻይና ባለሀብቶች ተመራጭ የሆነች የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗም ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የአገራቱን የሁለትዮሽ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ለማጠናከር ከቤጂንግ የንግድ ሙኒሲፓል ቢሮ በቅርበት እንደሚሰራ አስታውቋል።
የቤጂንግ የንግድ ሙኒሲፓል ቢሮ የውጭ ኢኮኖሚና የንግድ ዘርፍ ዳይሬክተር ዡዋንግ ጂያንሮንግ ኢትዮጵያ እምቅ የሆነ የኢንቨስትመንት አቅም እንዳላት ተናግረዋል።
የቻይና ባለሀብቶች የግብርና የቴክኖሎጂና የንግድ ዘርፎችን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።