AMN – ታኅሣሥ 10/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ሆስፒታሎች መካከል የትብብር፤ የመደጋገፍ የግብዓት ልውውጥ በማድረግ የኅብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ጥራት ለማሻሻል የሚያስችለው ፎረም መደበኛ ውይይቱን አካሂዷል።
በዚህ መደበኛ ውይይት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ ተገኝተው የፎረሙን ዋና ዓላማ ለመነሻነት አብራርተዋል።
በዚህም የአዲስ አበባ ሆስፒታሎች የልምድ ልውውጥ እና የድጋፍ ማዕቀፍ ዋና ዓላማው ጥራቱን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን ማሳደግ፣ በሆስፒታሎቹ መካከል የልምድ ልውውጥ፣ ቀጣይነት ያለው የትብብር ጥረቶች የጤና አጠባበቅ አቅርቦትን ደረጃዎች ለማጠናከር የሚረዳ ፎረም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የፎረሙ አባላት በየሁለት ሳምንቱ የፌደራል ሆስፒታሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ጤና ቢሮ ስር የሚገኙ የሆስፒታሎች ኃላፊዎችና ተወካዮች በተመረጡ ሆስፒታሎች በአካል በመገኘት እንደሚጎበኙ ተገልጿል።
ይህ የተቀናጀ አካሄድ የተለያዩ አገልግሎቶች በቀጥታ ለመመልከት እና ልምድ ለመቅስም ያስችላል እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር ደረጄ፣ በዚህም ጠቃሚ ትምህርቶችን እና ምርጥ ልምዶችን ለማውጣት ብሎም ለማስፋት እየረዳ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
የማህበረሰቡን ልዩ ልዩ የጤና ፍላጎቶች ለማሟላት በተሻለ ሁኔታ የተቀናጀ፣ ይበልጥ ጠንካራ እና ምላሽ ሰጪ የጤና አጠባበቅ ስነ-ምህዳር ማልማት እንደሆነ ነው የገለጹት።
ፎረሙ በሚያደርጋቸው የልምድ ልውውጥና የትብብር ሥራዎች በተመላላሽና በተኝቶ ክፍል ታካሚዎች፣ በፋርማሲ አገልግሎት፣ በምርመራ እና ላቦራቶሪ አገልግሎቶች፣ በታካሚ እንክብካቤ ላይ መሻሻሎችን እየተስተዋሉ እንደሆነም በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡
በውይይቱ ወቅትም የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት የፕሮግራም አፈጻጸም ግምገማ መደረጉን እና በቀጣይም በቋሚ አጀንዳነት እንደሚያዝ ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።