AMN-ኅዳር 16/2017 ዓ.ም
የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ረቂቅ አዋጅ በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብይት ሰንሰለትን የሚዘረጋ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና የዘርፉ ተዋናዮች ጋር ውይይት አድርጓል።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የህግ ዳሬክተር ሃብታሙ ሚልኪ፤ በ4 ክፍሎችና 28 አንቀጾች የተዋቀረውን አጠቃላይ የረቂቅ አዋጁን ይዘትና አስፈላጊነት በዝርዝር አቅርበዋል።
ከአስመጪው እስከ ተጠቃሚው ድረስ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ አስተማማኝ፣ ፍትሃዊና ተደራሽ የአቅርቦት፣ ስርጭትና የችርቻሮ የአሰራር ስርአትን መዘርጋት ማስፈለጉን ገልጸዋል።
በነዳጅ ውጤቶች የግብይት ሰንሰለት ውስጥ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ አሰራሮችና ተግዳሮቶችን ለመቆጣጠርና ግልጽና ቀልጣፋ አሰራሮችን ለመዘርጋት ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማትና ባለሙያዎች አለም አቀፍ ልምድ በሚጠይቀው መሰረት በሚፈለገው የብቃት ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን በማረጋገጥ ደህንነቱ የተጠበቀና ሕጋዊ የነዳጅ ውጤቶች የግብይት ስርአት ለመዘርጋት አዋጁ አስፈላጊ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
አስመጪ፣ አከፋፋይ፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፣ የነዳጅ ማደያ፣ አጓጓዥና የቀጥታ ተጠቃሚ ግዴታዎችና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲሁም የወንጀል ቅጣት በረቂቀ አዋጁ ተደንግጓል።
የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ማከማቸት፣ ከግብይት ስርአት ውጪ መሸጥ፣ ወደ ጎረቤት አገራት በኮንትሮባንድ ማጓጓዝና ሌሎች ህገ-ወጥ ተግባራትን መፈጸም የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት በረቂቅ አዋጁ በዝርዝር ተደንግጓል።
በውይይት መድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎች ከትርጓሜ፣ አገላለጽ እንዲሁም ለክልሎች የሚሰጥ ሃላፊነት በግልጽ መቀመጥ እንዳለበትና ወደ ዘርፉ ለሚገቡ አከፋፋዮች የሚጠየቁ መስፈርቶች ጠንከር ማለት እንዳለባቸው አንስተዋል።
ህገ-ወጥ ተግባር መፈጸም የሚያስከትለው የአስተዳደራዊና የወንጀል ተጠያቂነት የበለጠ ጠንካራ እንዲሆን መታየት እንዳለበትም አስተያየት ሰጥተዋል።
የተነሱ ሃሳብና አስተያየቶች ረቂቅ አዋጁን ለማዳበር በግብአትነት እንደሚወስዱ የሚመለከታቸው የመንግስት ሃላፊዎች በምላሽና ማብራሪያቸው አረጋግጠዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፤ ረቂቀ አዋጁ መንግስት በከፍተኛ ወጪ በሚያስገባቸው የነዳጅ ምርቶች ላይ የሚፈጸምን ሌብነት ለመቆጣጠር ያስችላል ብለዋል።
በነዳጅ ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከአዋጅ ማሻሻል በተጨማሪ ዘመናዊ አሰራሮች እየተዘረጋ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አስቻለው አላምሬ በአቅርቦት፣ ክምችትና ስርጭት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ፍትሃዊ የግብይት ስርአት ለመዘርጋት ረቂቅ አዋጁ ያለውን ጠቀሜታ አንስተዋለ።
የግብይት ሰንሰለቱን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ቀልጣፋ አሰራር በመዘርጋት ህገ-ወጥ ግብይትና በተደራሽነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ያግዛል ነው ያሉት።
በምክር ቤቱ የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አሻ ያህያ፤ የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ረቂቅ አዋጅ ለረጅም ጊዜ ማገልገል እንዲችል ከሚመለከታቸው አካላት የተለያዩ ውይይቶች እየተደረጉበት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!