የነገ ስንቅ

ሀገር የትውልድ ቅብብሎሽ ውጤት ናት። ችግኝ ተከላ ከማፍላት ጀምሮ እስከ መጽደቅ ድረስ ባለው ሂደት ጥንቃቄ የታከለበትና ሳይንሳዊ መንገድን የተከተለ ሲሆን ውጤቱ ያማረ እንደሚሆነው ሁሉ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ በተሻለ ሰብዕና ይታነጽ ዘንድ ዛሬ ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡ አዲስ አበባ ከዚህ አንጻር እያከናወነቻቸው ያሉ ስራዎች በበጎ ጅምርነት የሚታዩ እና በተሞክሮነት ሊወሰዱ የሚገባቸው ናቸው፡፡  

ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም “የነገ  ቀን”  በሚል  ተሰይሟል፡፡  እኛም ይህን  ቀን  መነሻ  በማድረግ  በአዲስ አበባ ከተማ ለነገዋ  ኢትዮጵያ የሚሆኑ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አስመልክቶ  ይህን ፅሁፍ  አዘጋጅተናል፡፡

ነገንም ጭምር ታሳቢ ያደረገው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም የሚሰጠው የህፃናት ማቆያ አገልግሎት

ለነገም ጭምር ዋጋቸው ትልቅ ከሆኑ ተግባራት መካከል የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም አንዱ ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም ህፃናት ከእናታቸው ማህፀን ካሉበት እስከ 6 ዓመት ያለውን የህፃናት የዕድገት ሂደት ያጠቃልላል። በዚህ ሂደትም የህፃናት አካላዊና አእምሯዊ እድገት ጤናማ እንዲሆን ተገቢውን እንክብካቤ ሊያገኙ ይገባል፡፡ በአካልና በአዕምሮ የበለፀገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ መገንባት ደግሞ ለነገ የማይባል የቤት ስራ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራምን አስመልክተው እንደገለፁት፤ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው፤ ነገር ግን በሰው ልጅ ህይወት ወሳኙ የሁለንተናዊ እድገት መሰረት የሚጣልበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡ ከተማ አስተዳደሩም ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ነው። በፕሮግራሙ 330 ሺህ ህፃናት ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ዛሬ ህፃናት ላይ መስራትና በሁለንተናዊ ድጋፍ ማሳደግ የነገ ሃገር ተረካቢ ትውልድ ላይ መስራት መሆኑን በመገንዘብ እንደ አዲስ አበባ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም በርካታ ስራዎች የተሰሩ መሆኑን የገለፁት ደግሞ ከጋዜጣው ዝግጀት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የቀዳማይ ልጅነት እድገት ክትትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ደረሰ ናቸው፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ ቢሮው በፕሮግራሙ የተለያዩ ስራዎች እየከወነ ነው፡፡ ህፃናት የሚያገኙት የተመጣጠነ ምግብ ለአካላዊ እና አእምሯዊ እድገታቸው ጠቃሚ በመሆኑ የቀጥታ አልሚ ምግብ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ በዚህም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ከ10 ሺህ 800 በላይ  በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ለተውጣጡ ነፍሰ ጡር እና ለሚያጠቡ እናቶች እንዲሁም እስከ ሶስት አመት ለሆኑ ህፃናት በየወሩ የቀጥታ አልሚ ምግብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡

የህፃናት የቀን ማቆያ ማእከላት ማስፋፋት ሌላው ተግባር ነው፡፡ በዚህም ማቆያ አቅም የሌላቸው ልጆቻቸውን ይዘው እንጀራ እየጋገሩ፣ አሻሮ እየቆሎ፣ ጉሊት እየሠሩ እየተቸገሩ ያሉ ሴቶች ወደተሻለ ስራ ገብተው ህይወታቸውን እንዲመሩ በመንግስት ወጪ ክፍያ በመፈፀም ለልጆቻቸው የቀን መዋያ ማዕከሉን እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው፡፡

ሌላኛው የህጻናት ማቆያ ላይ እየተሰራ ያለው ስራ ነው፡፡ በ350 የህፃናት ማቆያ ከ5 ሺህ 653 ህፃናት በላይ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ 108 የህፃናት መጫወቻ ስፍራዎች፣ እሁድ እሁድ በሚዘጉ መንገዶች እንዲሁም 185 አረንጓዴ ስፍራ ለህፃናት ተዘጋጅተው እንዲዝናኑ እየተደረገ ሲሆን፤ በዚህም በ2016 በጀት አመት 47 ሺህ ህፃናት ተጠቃሚ ሆነዋል ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ቢሮው በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም እያከናወነ ያለው ተግባር ለነገ ኢትዮጵያ ሃገር ተረካቢ ትውልድ የሚሆንና ተጠናክሮ የሚያስቀጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የነገን ኢትዮጵያ ስናስብ የዛሬን ህፃናት ማሰብ ነው፡፡ ዛሬ ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ አግኝተው በአካልና በአእምሮ ጎልብተው የነገ ሀገር ተረካቢ እንዲሆኑ የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡ ፕሮግራሙን ሁሉም አውቆ ለነገ ትውልድ የሚሆን ስራ እንዲሰራ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

የነገ ትውልድ ላይ እየተሰራ የመሆኑ ማሳያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እና ጎዳና ላይ ኑሯቸውን ያደረጉ ሴቶች የሚያገግሙበት የ“ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል” ነው። ማዕከሉ የተገነባው በዓመት 10 ሺህ የሚሆኑ በከተማ ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡና ጎዳና ላይ የሚኖሩ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በማለም ነው፡፡ 

ጉዳዩን አስመልክቶ ለዝግጅት ክፍላችን ማብራሪያ የሰጡት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሄርጳሳ ጫላ (ዶ/ር)፣ ሴቶችን የሚመለከቱ እና ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚተርፉ የልማት ስራዎች በመዲናዋ እየተከናወኑ ነው፡፡ ይህ ማዕከል በችግር ውስጥ ያሉ ሴቶች ነገ አዲስ ተስፋ በመሰነቅ ራሳቸውን ችለው የሚኖሩበትን ሁኔታ የሚያመቻች ነው ብለዋል፡፡

“ለነገዋ” የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል

ሄርጳሳ (ዶ/ር) አክለውም፤ ሴቶች በሌሉበት ማንኛውንም ልማትና እድገት ማሰብ አይቻልም፡፡ ሴቶች በሃገሪቱ ልማት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ከፍተኛ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአመራርነት ደረጃም ይሁን በሌሎች መስኮች ውጤታማ ስራዎችን እየሠሩና ለሃገራቸው አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው፡፡ ትውልድን የሚያስቀጥሉ፣ ልማት፣ እድገትና ብልፅግናን የሚያረጋግጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሆናቸው በማእከሉ የሚገቡ ሴቶች ይህን እውን የሚያደርጉ እንዲሆኑ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

ማእከሉ በብዙ ውጣ ውረድ እና የህይወት ፈተና ውስጥ የነበሩ ሴቶች ነገን በተስፋ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ መኖር እንዲችሉ የሚያደርግ ነው፡፡ ለጎዳና ህይወት የተዳረጉ እና በአስከፊ ችግር ውስጥ የሚኖሩትን ካሉበት ችግር ተላቅቀውና የራሳቸውን ገቢ አግኝተው ኑሯቸውን እንዲኖሩ እየተሰራ ነው። ከጠባቂነትና ከተረጂነት ስሜት እንዲላቀቁ ተገቢውን የተሃድሶና ተግባራዊ የሙያ ክህሎት ስልጠና እየተሰጣቸው ነው፡፡ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ህይወታቸው እንዲሻሻል ከማስቻል ባለፈ በሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ የራሳቸው አበርክቶ እንዲኖራቸው እድል የሚፈጥርላቸው እንደሆነም ተናግረዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ አዲስ አበባ የያዘችው የልማት ጉዞ ለሌሎች የሀገሪቱ እና የአፍሪካ ከተሞች ምሳሌ ወደ መሆን እየሄደች ነው፡፡ የነገዋ ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ህብረተሰብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ፣ የሥራ እድል የሚፈጥሩ፣ የእውቀት ሽግግር የሚደረግባቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ይህ ማእከል ተጠቃሽ ነው፡፡ በችግር ውስጥ የሚኖሩ በርካታ እህቶቻችንን ወደተሻለ የህይወት ጎዳና የሚመልስ በመሆኑ ለነገ ስንቅ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት አሁን ላይ መሰራቱ ለነገዋ ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋን በማምጣት እና ከጥገኝነት በመላቀቅ ስራ ፈጣሪ ትውልድ እንዲፈጠር አስተዋፅዖ አለው፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ የዓድዋ ድል መታሰቢያ አዲስ አበባ ለነገዋ ኢትዮጵያና ለትውልድ መሰረት የሚሆን ስራ እየሰራች የመሆኗ ማሳያ ነው፡፡ የወል ታሪካችን ማሳያ ሆነውን የዓድዋ ድል ወቅቱን የሚመጥን እና ለቀጣዩ ትውልድ የአርበኝነት እና የመረጃ ስንቅ የሚሆን ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ ቁልፍ ሚና ያለው የኮሪደር ልማት አስደማሚ የሆነ ውጤት የታየበት እና ነገ ላይ እየተሰራ የመሆኑ ነጸብራቅ ነው፡፡ ምቹ የሆነ ከባቢን፣ አረንጓዴ ስፍራ፣ ደረጃውን የጠበቀ የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገድ፣ የህዝብ መዝናኛ ስፍራ፣ የህዝብ መፀዳጃ ቤትና ሌሎችን አካትቶ የተሰራው የኮሪደር ልማት ስራ ለነገው ትውልድ የስራ ባህልን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ነገሮችን የሚያወርስ ስለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡

የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብርም እንዲሁ ሰው ተኮርና ለነገ ኢትዮጵያ ግንባታ የሚተርፍ ተግባር የተከወነበት ነው፡፡ በዚህ መርሃ ግብር የዕለት ጉርስ ማግኘት አቅቷቸው ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ የከተማዋ ህፃናት አጉራሽ ያገኙበት ነው፡፡ በዚህም መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በ2016 የትምህርት ዘመን በመንግስት ትምህርት ቤቶች 779ሺህ በላይ ተማሪዎች ቁርስና ምሳ በመመገብ ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካም መዲና ናት፡፡ ከዚህ አኳያ በአሁኑ ወቅት ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ እየተከናወኑ ያሉ ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎች ለኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ለአፍሪካ ነገ እየሰራች መሆኗን የተግባር አስረጅዎች ናቸው፡፡ የማህበረሰቡን በተለይ የወጣቱን ሀገር ተረካቢነት የሚያፀኑ ስራዎች መሰራታቸው ትልቅ የእድገት እምርታ ላይ እንደምትገኝ ማሳያ ናቸው የሚሉት ደግሞ የታሪክና የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ ሰይድ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

አዲስ አበባ የጀመረችው የልማት ጉዞ ሊቀጥል ይገባል፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ መስኮች እያከናወነች ያለችው የልማት ትሩፋት ለነገ ትውልድ፣ ለነገ ኢትዮጵያ የሚተርፉ ናቸው፡፡ ዛሬ ላይ የሚከናወኑ ስራዎች ዘመንን ተሻግረው ለነገ የሚጠቅሙና ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸው መሆን ስላለባቸው በተጀመረው መንገድ በትኩረት ነገን ታሳቢ ተደርገው መሰራት አለባቸው፡፡ የአፍሪካ መዲናና የተለያዩ ዲፕሎማቶች መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ እንደ ስሟ አበባነቷን ይዛ መቀጠልና ለህዝቦች ተጠቃሚነትና ለነገዋ የበለፀገች ኢትዮጵያ መሰረት በመሆኗ ከዚህ የበለጠ በትጋት መስራትን እንደሚጠይቅ ይናገራሉ፡፡

ሰይድ (ዶ/ር) አያይዘውም፤ ሀገሩን የሚወድድ፣ መልካም ስነ ምግባርና ጠንካራ የሥራ ባህል ያለው ትውልድ ሲፈጠር ሃገር በሚፈለገው የዕድገት ጎዳና ትራመዳለች፡፡ ኢትዮጵያ ባሏት በርካታ ሀገር በቀል እውቀቶች መጠቀም ከቻለች ጠንካራና በስነ ምግባር የታነጸ፣ ለሀገሩ ልማት የበኩሉን አሻራ የሚያስቀምጥና የሚተጋ ትውልድ መፍጠር ይቻላል፡፡ በመሆኑም ወጣቶች ላይ በመስራት ለነገዋ ኢትዮጵያ መደላድል ማስቀመጥ ያስፈልጋል ሲሉ ምክረ ሀሳባቸውን አስቀምጠዋል፡፡

በሰገነት አስማማው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review