AMN – ጥቅምት 4/2017 ዓ.ም
የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን መቋቋም በተፋሰሱ ሃገራት መካከል የህግ ማዕቀፍ እንዲኖርና ሃገራቱ በትብብር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን የህዳሴ ግድብ አለም አቀፍ ተደራዳሪና የውሃ ፖለቲካ ተማራማሪ ፕሮፌሰር ያቆብ አርሳኖ ገለጹ፡፡
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ተግባራዊ እስኪሆን ለአስራ አንድ አመታት በተፋሰሱ ሃገራት ድርድር ሲካሄድበት መቆየቱ ይታወሳል፡፡
አሁን ላይ የማዕቀፍ ስምምነቱን አብዛኛዎቹ ሃገራት ያጸደቁት ሲሆን ስድስቱ ሃገራት ደግሞ የህጋቸው አካል ማድረጋቸው የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን እንዲቋቋም አስችሏል፡፡
የኮሚሽኑ መቋቋም ሃገራቱ በትስስርና በትብብር ተጠቃሚነታቸው እንዲያድግና ህጋዊ መሰረት የሚጥል ስለመሆኑ የህዳሴ ግድብ አለም አቀፍ ተደራዳሪና የውሃ ፖለቲካ ተማራማሪ ፕሮፌሰር ያቆብ አርሳኖ ተናግረዋል፡፡
በማዕቀፍ ስምምነቱ ውስጥ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ከመሆኗ ባሻገር ከፍተኛ የዲፕሎማሲና የዕውቀት ሽግግር ተግባር ማከናወኗን ፕሮፌሰር ያቆብ ገልጸዋል፡፡
ማዕቀፉን ያልፈረሙ ሃገራት ያስተሳሰራቸውን የተፈጥሮ ሃብት በፍትሃዊነት ለመጠቀም ወደ ህግ ማዕቀፉ መግባት ግድ እንደሚላቸውም አስታውቀዋል፡፡
በተፋሰሱ ሃገራት የተቋቋመው ኮሚሽን ለቀጣናው አሉታዊ አቋም ያላት ግብጽን ስርዓት ሊያስይዛት ያስችላል ያሉት ፕሮፌሰሩ ሃገሪቱ አሁን የያዘችው አቋም አያዋጣትምም ብለዋል፡፡
በዝናሽ ሞዲ