“የንብረት ማስመለስ አዋጅ መፅደቅ ጤናማ የሆነ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት እንዲኖር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው” -አቶ በላይሁን ይርጋ

You are currently viewing “የንብረት ማስመለስ አዋጅ መፅደቅ ጤናማ የሆነ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት እንዲኖር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው” -አቶ በላይሁን ይርጋ

AMN-ጥር /2017 ዓ.ም

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ የንብረት ማስመለስ አዋጅን፣ አዋጅ ቁጥር 1364/2017 አድርጎ አጽድቋል።

የአዋጁ መፅደቅ ለወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርዓቱ እና ለፋይናንስ አስተዳደር ስርዓቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የአ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የመንግስት ሕግና ፍትህ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ ገልጸዋል፡፡

የአዋጁ ዋነኛ ዓላማ የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችንና ገንዘቦችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመያዝ፣ ለማገድ፣ ለመውረስ ወይም ለማስተዳደር የሚያስችል ግልጽና ዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ በማበጀትና ማንም ሰው ከሕገ-ወጥ ድርጊት ማናቸውንም አይነት የኢኮኖሚ ጥቅም እንዳያገኝ ለማድረግ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

እንዲሁም የንብረት ማስመለስ ሕግ ወንጀልን በመከላከል ሂደት ያለውን ከፍተኛ ሚና ለማሳካት የሚያስችል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የዚህ አዋጅ መፅደቅ ከወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርዓቱም በተጨማሪ ጤናማ የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት እንዲኖርም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ ገልጸዋል፡፡

የንብረት ማስመለስ ሕግ ለኢትዮጵያ ወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርዓት አዲስ አለመሆኑን ነው የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው።

ከወንጀል ጋር ግንኙነት ያለውን ምንጩ ያልተወቀ ንብረትን ማስመለስ እንዲቻል እና በተለያዩ ሕጎች ውስጥ ተበታትነውና ለአፈጻጸም አስቸጋሪ ሆነው ያሉትን የንብረት ማስመለስ እና መውረስ መሠረታዊ ድንጋጌዎች እና የሥነ-ሥርዓት ሂደቶች የንብረት ማስመለስና መውረስ ሂደት ውስጥ ያሉትን ልዩ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሁሉም አይነት ወንጀሎች የሚያገለግል አንድ ወጥ የሆነ ዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ በማውጣት በንብረት ማስመለስና መውረስ ሂደት ውስጥም ሆነ ንብረቱ ከተወረሰ በኋላ የንብረቱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ ተዘጋጅቶ የፀደቀ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

አዋጁ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ሲደረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ ራሱን የቻለ ማስፈጸሚያ እቅድ እና ዝርዝር የአሰራር ስርዓት እየተዘጋጀ መሆኑን ሚኒስትር ዲኤታው መናገራቸውን የፍትህ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review