AMN-ኅዳር 18/2017 ዓ.ም
የንግድ ፈጠራ ስራ ባለቤቶችን የማጠናከርና የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
ዓለም አቀፍ የንግድ ስራ ፈጣሪዎች (ኢንተርፕርነርሺፕ) ሳምንት “ኢንተርፕርነርሺፕ ለሁሉም” በሚል መሪ ሃሳብ ከጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ሲካሔድ ቆይቷል።
የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንቱ በአለም ለ16ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ10ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ አካላት በቀጥታ እና በበየነ መረብ ተሳትፈዋል፡፡
የፓናል ውይይቶች፣ አውደርዕዮች፣ ኮንፈረንሶች፣ ሴሚናሮች፣ የእርስ በእርስ ትውውቅና የልምድ ልውውጦች የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንቱ አካል ነበሩ፡፡
የበዓሉ የመዝጊያ ፕሮግራም የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በተገኙበት ትናንት ማምሻውን ተከናውኗል።
በመድረኩ በተለያዩ የስራ ፈጠራ ዘርፎች ተወዳድረው ብልጫ ያስመዘገቡ የዓመቱ ምርጥ ስራ ፈጣሪዎች ከስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እውቅና ተበርክቶላቸዋል።
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በምታደርገው ርብርብ የኢንተርፕርነሮች ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
በርካታ የዓለም አገራት ችግሮችን ተሻግረው ከሐብት ማማ ላይ የደረሱት ለስራ ፈጠራ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከለውጡ ወዲህ መንግስት ለስራ ፈጠራ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱንና በዚህም አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።
ዜጎች ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበትና የፋይናንስ ክፍተቶቻቸውን የሚሞሉበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ነው ያስረዱት፡፡
አሁን ላይ በርካታ ዜጎች ከስራ ጠባቂነት ወደ ስራ ፈጣሪነት በመሸጋገር ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች አማራጭ የስራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን አመላክተዋል።
በቀጣይም የንግድ ፈጠራ ስራ ባለቤቶችን የማጠናከርና የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
እውቅና የተሰጣቸው አካላት በቀጣይም ጠንክረው በመስራት የድርሻቸውን አገራዊ ሃላፊነት እንዲወጡም አደራ ብለዋል።
የዜጎችን የስራ ፈጠራ ከህሎት በስልጠና በማጎልበት ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ሚና ጉልህ እንደነበር መጥቀሳቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!
All reactions:
1111