ባህል አንድ ማህበረሰብ እምነቱን፣ ፍልስፍናውን፣ ጥበቡን እና ሁለንተናዊ አስተሳሰቡን፣ እሴቶቹንና የመሳሰሉትን የሚያንጸባርቅበት ትልቅ ሀብቱ ነዉ። ባህል ከሰው ልጅ አኗኗር ጋር የተያያዘና የማኅበረሰብ ዕድገት ውጤት ነው፡፡ የሁሉም ሥልጣኔና ዕድገት ምንጩ ከማኅበረሰቡ ባህል ነው የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብም ከዕለት ተዕለት አኗኗሩ የዳበረና የበለፀገ ባህል፣ እሴትና ታሪክ ያለው ህዝብ ነው፡፡ ይህ ህዝብ ካለው አኩሪና ቀደምት ባህሎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ኢሬቻ ነው፡፡
ኢሬቻ ለአምላክ የሚቀርብ የምስጋና ስርዓት ነው፡፡ ለአንድ አምላክ፣ የሁሉ ፈጣሪ ለሆነ እሱ የፈጠረውን (ለምለም) ይዘው የሚያመሰግኑበት ስርዓት ነው፡፡ ይህ የኦሮሞ ህዝብ የምስጋና ስርዓት የዳበረ ባህላዊ እሴት አዲሱ ትውልድና ዓለምም ሊማርበት የሚችል በርካታ ቁም ነገሮች እንዳሉት ከኦሮሞ ጥናት ማዕከል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢሬቻ የሚካሄድበት ማንኛውም ቀዬ፣ ሐይቅ ወይም ስፍራ የሰላምና የእርቅ ስፍራ ነው፡፡ በንፁህ ልብ፣ ያላንዳች ቂምና በቀል ሠላምና እርቅን የሚያውጁበት ነው፡፡ ቂምና በቀል፣ አለመግባባትና ጥላቻ ያለው ማንኛውም ግለሰብ ጥላቻውን ሳይሽር፣ እርቅ ሳያወርድ፣ የገደለ ሳይክስ፣ እጁ ንፁህ ያልሆነ ግለሰብ ወደ ኢሬቻ አይሄድም፡፡ እንደ የኦሮሞ ህዝብ ባህልም የተከለከለ ነው፡፡ ኢሬቻ ከመድረሱ በፊት አባ ገዳዎች በየአካባቢያቸው በየደረጃው ባለው መዋቅር ያለውን ችግር ይፈታሉ፤ የተጣላውን ያስታርቃሉ፤ የገደለ እንዲክስ ያደርጋሉ፡፡ ይህም የሚሆነው ሠላምና እርቅ ኢሬቻ ካለው እሴት መካከል አንዱ ስለሆነ ነው ይላል መረጃው፡፡

ስለዚህ የኢሬቻ ዕለት ሠላም ይታወጃል፤ ይወደሳል፡፡ በኢሬቻ በዓል ስለ ሠላም ይሰበካል፡፡ ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት፣ ከሰፊው ህዝብ፣ ከፈጣሪና ከፍጡር ጋር በሠላም አብሮ መኖር እንደሚገባ ይታወጃል፡፡ የኢሬቻ በዓል የፈጣሪና የፍጡር እርቅ የሚለመንበት ስፍራ ነው፡፡ የኢሬቻ ስፍራ ህዝቡ ስለ ጥፋቱና ስለ በደሉ ፈጣሪውን ይቅርታ የሚጠይቅበት የእርቅ ስፍራ ነው፡፡ ሳያስቡ የተጋጩ ሰዎች እንኳን እርቅ የሚያወርዱበት ነው፡፡ ስለዚህ ኢሬቻ የእርቅና የአምላክ ምህረት የሚወርድበት ስፍራ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ የኦሮሞ ህዝብ “ሰው እርስ በርሱ ከታረቀ ፈጣሪም ይታረቃል” የሚለ አባባል እንዳለውም የኢሬቻ ባህላዊ እሴቶችን አስመልክቶ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የማይዳሰሱ ቅርሶች ተመራማሪ አቶ ገዛኸኝ ግርማ ገልፀዋል፡፡
የኢሬቻ ቦታ ለይቅርታ ትልቅ ስፍራ ያለው ነው፡፡ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ፣ ሳያስቡበት በድንገት አለመግባባት ተፈጥሮ ከሆነ የተፈጠረ ቅሬታ ካለ በኢሬቻ ዕለት ይቅር መባባል ትልቁና ዋነኛው የኢሬቻ ተምሳሌት ነው፡፡ እንደ ኢሬቻ ባህል አለመግባባትና ቅሬታ ያለው አስቀድሞ ይቅር በመባባል በንፁህ ልቦናና አእምሮ ወደ ኢሬቻ ስፍራ መሄድ አለበት፡፡ ኦሮሞ “በንፁህ ልቦና ወደ ንፁህ መልካ ይወረዳል” ብሎ በምሳሌው የሚናገረውም ለዚህ ነው፡፡ አባ ገዳው በኢሬቻ ስፍራ “ቅራኔ ያላችሁ ዛሬውኑ ይቅር ተባባሉ” ብሎ የሚያውጀውም ለዚህ እንደሆነ ከኦሮሞ ጥናት ማዕከል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዮሴፍ ሙለጌታ ባባ (ዶ/ር) ኢሬቻን አስመልክቶ በይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጥናታዊ መጣጠትፍ እንደገለፁት ኢሬቻ የምስጋና፣ የእርቅ፣ የአንድነት፣ የሠላም እና የደስታ በዓል ነው፡፡ ቂም ተይዞ ወደ ኢሬቻ አይኬድም! ኢሬቻ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ እንደ ቅዱስ በዓል ይከበራል። የመልካም ነገሮች ሁሉ ምንጭ ዋቃ ነው፡፡ ሕዝቡ ለዚህ መልካም ስጦታ ከልብ የመነጨ ምስጋና ለአምላኩ የሚያቀርብበትና “የዋቃዮ ስጦታ ተመልሶ ለዋቃዮ የሚሰጥበት ቅዱስ በዓል ነው” ብሎ ከልቡ ያምንበታል። ስለዚህ ኢሬቻ ማለት “ስጦታ” ማለት ነው ይላሉ።
በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ለምለም ሣር የሰላምና የብልጽግና ምልክት በመሆኑ፣ በኢሬቻ በዓል ላይ የሚሳተፈው እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ይህንን ለምለም ሣር በሁለት እጆቹ በመያዝ አምላኩን ያመሰግናል። ከሁሉም በላይ ክረምቱን ከበረዶ፣ ከከባድ ነፋስ፣ ከጎርፍና ከውርጭ የታደጋቸውን ታላቅና ቅዱስ አምላካቸውን አንድ ላይ ሆኖ ያመሰግናሉ። መኸሩንና አዝመራውን ደግሞ እንዲባርክላቸው ወደ ፈጣሪ ይጸልያሉ። ስለዚህ የኢሬቻ በዓል ከጨለማ ወደ ብርሃን ላሻገረ አምላክ የሚሰጥ የክብር ዋጋ ነው።
የገዳ ስርዓት የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ዩኔስኮ) ቅርስነት ከተመዘገበ ወዲህ የኢሬቻ በዓል የኦሮሞና የአገሪቷ ከመሆን አልፎ ዓለም አቀፍ ለመሆን እንደበቃም ይነገራል፡፡ ይህ ደግሞ ወንድማማችነትና ከብሔር ብሔረሰቦች ጋር መቀራረብ፣ በህዝቦች መካከል መተማመን እንዲኖር በማድረግ ለሀገር ሠላም ዋስትና በመሆን የተረጋጋች አገር በመገንባት ሂደት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ይነገራል፡፡
የኢሬቻ ስፍራዎች በፍቅር የተሞሉ ናቸው፡፡ ኢሬቻ ፍቅር የሚሰበክበት ስፍራ ነው፡፡ በኢሬቻ ፈጣሪ ከፍጡር ጋር እንዲስማማ፣ ትልቅ ከትንሹ፣ ሀብታም ከድሃው፣ ጎረቤት ከጎረቤት፣ ጎረቤት ከአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ማኅበረሰብ ከማኅበረሰብ፣ አገር ከዓለም ጋር በፍቅር አብሮ እንዲኖር የሚሰበክበት ስፍራ ነው፡፡
ኢሬቻ ካሉት እሴቶች መካከል ተስፋና መልካም ምኞት አንዱ ነው፡፡ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የፀደይ (የብራ) ወቅት ብሩህና የደስታ ወቅት ነው፡፡ የመላው ኦሮሞ ቀዬ፣ ጓዳውና አካባቢው በተስፋና በመልካም ምኞት የሚሞላበት ወቅት ነው፡፡ በፀደይ (በብራ) ወቅት ዘመድ ከአዝማዱ ያለ ምንም ችግርና ሀሳብ ከያለበት ተሰባስቦ የሚጠያየቅበት፣ የተዘራው በቅሎ የሚያብብበት፣ ያበበው አሽቶ መልካም ፍሬ የሚያፈራበት፣ ያፈራውም የሚበላበት ወቅት ነው፡፡ ፀደይ (ብራ) መልካም ሽታ ያለው፣ ለማንኛውም ማኅበራዊ እንቅስቃሴ የሚመች፣ የተስፋና የምኞት፣ ጥጋብና ብልፅግና የሚሰበክበት ወቅት ነው፡፡
በኢሬቻ ቀን ላለፈው ምስጋና ይቀርባል፣ ለወደፊቱ ተስፋ ይሰነቅበታል፡፡ እነዚህ ሁለቱ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ አገር አስፈላጊ እሴቶች ናቸው፡፡ ይህም ኢሬቻ የወደፊት ተስፋና መልካም ምኞት የሚያመላክት መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ኢሬቻ በገዳ ሥርዓት እሴቶች የሰላምና የአንድነት ተምሳሌት ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ሁሉን ነገር ለፈጠረው፤ ምድርንና ሰማይን፣ ወንዝንና ባህርን፣ ቀንንና ሌሊትን፣ ብርሃንና ጨለማን፣ ሕይወትና ሞትን፣ ክረምትንና በጋን፣ ዝናብንና ሐሩርን፣ እጽዋትን፣ እንስሳትንና ሰውን ለፈጠረ፤ ሁሉን ነገር ማድረግ ለሚችል ዋቃ (አምላክ) ምስጋናና ክብር የሚያቀርብበት ሥርዓተ በዓል ስለመሆኑም ይነገራል።
አቶ ገዛኸኝ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ እጅግ የበለፀገች ሀገር ናት ብለው፣ እንደ ኢሬቻ፣ ፍቼ ጨምበላላ፣ የጥምቀት ክብረ በዓል እና የመስቀል በዓላት የመሳሰሉ ህዝቦችን የሚያቀራርቡ፣ የሚያስተዋውቁ፣ በአንድነት ተከባብረውም ለመኖር የሚያግዙ ቅርሶች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
አክለውም በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ በሚከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ የበዓሉ ተሳታፊዎች እርጥብ ሳር እና አደይ አበባን በእጃቸው በመያዝ በወንዙ ወይም በሐይቁ ዳርቻ በማስቀመጥ ፈጣሪያቸውን ከጨለማው ክረምት ወደ ፀደይ ስላሻገራቸው ምስጋና የሚያቀርቡበት ነው፡፡ በዚህ በዓልም የኦሮሞ ህዝብም ሆነ ሌሎች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በባህላዊ ልብስ አጊጠው ወደ በዓሉ ስፍራ እንደሚሄዱም ጠቅሰዋል፡
ይህም የራሱ ሆነ ስርዓት ያለው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ገዛኸኝ፣ እናቶች ከፊት፣ ከእናቶች መካከል አንጋፋ የሆኑት ጫጩና ሲንቄ ይዘው ወደ ክብረ በዓሉ ይሄዳሉ፡፡ አባ ገዳዎችም እንዲሁ በግንባራቸው ላይ የሉዓላዊነት ምልክት የሆነውን ከለቻ ያስራሉ፡፡ በእጃቸውም ቦኩ ይይዛሉ። በበዓሉ የሚታወቀውን የምስጋና ዜማ “መሬ ሆ” በማለት ያዜማሉ፡፡ ይህም በዓሉ በየአመቱ ሳይቋረጥ ይምጣልን ማለት ስለመሆኑም አቶ ገዛኸኝ ተናግረዋል፡፡
ኢሬቻ ከኦሮሞ ህዝብ ባሻገር የተለያዩ ህዝቦች የሚሳተፉበት በዓል ነው፡፡ በመሆኑም ኢሬቻ የህዝብን ግንኙነት በማጎልበት፣ እርስ በእርስም ተከባብሮ የመኖር ባህልን በማጠናከር ትልቅ እሴት ያለው እንደሆነም አቶ ገዛኸኝ ይገልፃሉ፡፡
ኢሬቻ በሆራ ፊንፍኔም መከበሩ ለቅርሱ መጠበቅ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ገዛኸኝ እነዚህን በዓላት በደመቀ መልኩ የተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማክበር መቻላቸው አንዱ የሌላውን ባህል እንዲያውቅና አንድነታችን የበለጠ እንዲጠናከር የሚያግዝ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
ለስልሳ ዓመታት ገደማ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ታሪክና ባህል፣ የእርስ በእርስ ትስስርና አብሮነታቸውን በሚመለከት የተለያዩ መፃህፍትና በርካታ ጥናቶችን በማሳተም የሚታወቁት አሜሪካዊው የሶሺዮሎጂ ምሁር ዶናልድ ሌቪን (ፕ/ር) ታላቋ ኢትዮጵያ ‘Greater Ethiopia’ በተሰኘው መጽሃፋቸው የኢትዮጵያውያን የቋንቋና የአካባቢ ድንበር ሳይጋርዳቸው በጥልቅ የተሳሰሩባቸው ዕሴቶች ያሏት፣ ተናፋቂና ውብ ሀገር ስለመሆኗ መስክረዋል፡፡
ለአብነትም ኃይማኖታዊ በዓላትና አከባበራቸው በተለያዩ አካባቢዎች ተቀራራቢ መሆኑ፣ ሁሉም ሰላምን፣ ፍቅርን፣ እርቅንና አብሮነትን የሚያስተምሩ መሆናቸው ደግሞ ኢትዮጵያውያን በረዥም ዓመታት የገነቡት የጥልቅ እሴት ውጤት መሆኑን ምሁሩ ያሰምሩበታል። እንደ መስቀልና ኢሬቻ ያሉ በዓላት ኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና በተደቀነባት ጊዜያት ሳይቀር አንድነቷ ተጠብቆ እንዲቀጥል ሚናቸው ጉልህ መሆኑንም በመጽሃፋቸው በስፋት አብራርተዋል፡፡
በመለሰ ተሰጋ