የአማራ ክልል በተሻለ የሰላምና ልማት ጉዞ ላይ ይገኛል – የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

You are currently viewing የአማራ ክልል በተሻለ የሰላምና ልማት ጉዞ ላይ ይገኛል – የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

AMN-ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም

የአማራ ክልል ከመቼውም ጊዜ በላይ በተሻለ የሰላምና ልማት ጉዞ ላይ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ተናገሩ።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ፤ በክልሉ ተፈጥረው የነበሩ የሰላምና የጸጥታ ችግሮች በዋናነት ከፖለቲካዊ ጽንፈኝነት ጋር የተያያዙ እንደሆኑ አስታውሰው፤ በወቅቱ አመራሩ በሚጠበቅበት ልክ ችግሩን ታግሎ በማስተካከል ረገድ ለዘብተኛ አቋም መውሰዱም ተናግረዋል።

በዚህም ጽንፈኛ ቡድኖች በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት ማድረሳቸውን ጠቁመዋል።

መንግስት በክልሉ ሰላምን በማስፈን ረገድ ማህበረሰቡን በማሳተፍ ውጤታማ ስራ ማከናወኑንም ተናግረዋል።

የክልሉ ነዋሪዎችም የጽንፈኛ ቡድኑን ትክክለኛ ማንነት ተገንዝበው ከመንግስት ጎን በመሆን ለዘላቂ ሰላም የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ክልሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በተሻለ የሰላምና የልማት ጉዞ ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

በክልሉ የተገኘውን ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ በመንግሥት በኩል ሁለት የመፍትሄ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን አስረድተዋል።

የመጀመሪያው ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ መንግስት ዘወትር ለሰላም በሩን ክፍት አድርጎ እየሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በሌላ በኩል የቀረበውን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን በመተው የክልሉን ሰላም ለማወክ በሚሰሩ ጽንፈኛ ቡድኖች ላይ መንግስት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።

የአማራ ክልል ሕዝብ በቀጣይ ሰላምን በማስጠበቅ በኩል ከመንግስት ጎን በመሆን የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review