የአምራችና ሸማች ትስስር ለገበያው ሚዛናዊነት

You are currently viewing የአምራችና ሸማች ትስስር ለገበያው ሚዛናዊነት



·        ከተማ አስተዳደሩ በ2017 በጀት ዓመት 854 ሺህ 327 ኩንታል የሚሆን የምርት ግብይትን   ለማስተሳሰር አቅዷል

የከተማ ነዋሪ በአብዛኛው “ሸማች” ነው። ከሚሸምታቸው ምርትና አገልግሎቶች መካከል ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ መሠረታዊ ምርቶች ሰፊውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ እነዚህ ምርቶች ደግሞ ምንጫቸው የግብርና ምርትን ከሚያመርቱ አርሶ አደሮች እንዲሁም የግብርና ምርቶችን በግብዓትነት ተጠቅመው በማቀነባበር ወይም እሴት በመጨመር ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ናቸው፡፡ አምራቾች በአብዛኛው መገኛቸው ከከተሞች ወጣ ባሉ አካባቢዎች ነው። ይህ ደግሞ በአምራች እና ሸማቹ መካከል የሚፈጠረውን የግብይት መስተጋብር የተለያየ ገፅታ እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ በአምራች እና በሸማች መካከል ደላሎች እንዲገቡ ክፍተት ይፈጥራል። የገበያው ሁኔታ ከአምራቹ እና ሸማቹ ውጪ ባለ ሦስተኛ አካል እንዲዘወር ያደርጋል። የገበያው አጠቃላይ አውድም ይታወካል፡፡ ሁኔታው እየተስፋፋ ሲሄድ በሕዝብ፣ በመንግስት እና በአገር ላይ የበረታ ተፅዕኖ ወደማሳረፉ ይደርሳል፡፡

የዓለም ተሞክሮ እንደሚያሳየን፤ የከተሞች የሸማችነት ሚና ወደ አምራችነትም እየተሸጋገረ መሆኑን ነው፡፡ ለዚህ ብዙ አብነቶችን ማንሳት የሚቻል ቢሆንም፤ ባሕር ሳናቋርጥ፣ አድማስ ሳንሻገር እዚሁ መዲናችን ውስጥ ያለውን የአምራችነት ጅምር እንቅስቃሴ መመልከት ይበቃል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ ከታዩ በጎ የሥራ እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ የከተማ ግብርና ስለመሆኑ አያጠያይቅም። ከዓመት ዓመት መሻሻሎችን እያሳየ የመጣው የመዲናዋ የከተማ ግብርና እንቅስቃሴ፤ ዜጎች ባላቸው ውስን ቦታ፣ በሚጠቀሙት ቴክኖሎጂ፣ ወደ ተግባር በሚለውጡት የፈጠራ ብቃት ታግዞ እና መንግስት በሚሰጠው ድጋፍና ማበረታቻ ተጠናክሮ ዛሬ ላይ ከራስ ፍጆታ አልፎ ለገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን በብዛት ማምረት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ይህ ብቻውን ግን የአዲስ አበባን የመሠረታዊ ምርቶች የግብይት ሁኔታ ለማረጋጋት በቂ አይሆንም፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ካሉ አምራች የአገሪቷ አካባቢዎች ምርቶችን በብዛት እና በዓይነት ማስገባት እና ለሸማቹ ማሰራጨት ይገባል፡፡ ይህንን ሚና ለመወጣት ደግሞ የሸማች ህብረት ሥራ ተቋማት ኃላፊነት ወሳኝ ነው፡፡

የሸገር የከተማ ግብርና ህብረት ሥራ ማህበር ተመስርቶ በይፋ ወደ ሥራ የገባው በ2014 በጀት ዓመት ሲሆን፤ 62 አባላት አሉት፡፡ ዋና ተግባሩም፤ ከአምራች አርሶ አደሮች እና ከአባላቱ የግብርና ምርቶችን በማሰባሰብ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ለሚገኙ የሸማች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች መሸጥ ነው፡፡ በዚህም ተግባሩ የማህበሩን አባላት እና አምራች አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ከማድረጉ ባሻገር የግብይት ስርዓቱን በማረጋጋት ለመዲናዋ ሸማች ማህበረሰብ እና ለአስተዳደሩ ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ በሠራው በጎ ሥራም የከተማ አስተዳደሩ ህዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም ባዘጋጀው መድረክ ዕውቅናና ምስጋና ችሮታል፡፡

አቶ ኡካ ገመቹ፤ የሸገር የከተማ ግብርና ህብረት ሥራ ማህበር ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ስለማህበሩ የሥራ እንቅስቃሴ እና በከተማዋ የምርት አቅርቦት ሂደት ላይ እያበረከተ ስላለው አስተዋፅኦ በተመለከተ፤ “በዋናነት የግብርና ምርቶችን በማቅረብ ሥራ ላይ የተሰማራው ማህበሩ፤ ከሚያቀርባቸው ግብርና ምርቶች መካከል፡- ጤፍ፣ አተር ክክ፣ ምስር ክክ፣ ጥራጥሬ እና አትክልቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ማህበሩ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የሸማች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች ምርቶችን እያቀረብን እንገኛለን፡፡ ምርታችንን በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የሸማች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች በስፋት የማቅረብ አቅማችንና ተደራሽነታችን ከዓመት ዓመት እያደገ መጥቷል፡፡ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት ብቻ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለሚገኘው የአቃቂ ቃሊቲ ሸማች ህብረት ሥራ ዩኒየን 1 ሺህ ኩንታል ደረጃ አንድ የሆነ ጤፍ፣ በልደታ ክፍለ ከተማ ለሚገኘው የልደታ ፋና ሸማች ህብረት ሥራ ዩኒየን ከ1 ሺህ 9 መቶ ኩንታል በላይ ጤፍ፣ አተር እና ምስር ክክ እንዲሁም የጥራጥሬ ምርቶች፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ለሚገኘው የምዕራብ ሸማች ህብረት ሥራ ዩኒየን፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ ለሚገኘው የአጋር አራዳ ሸማች ህብረት ሥራ ዩኒየን የተለያየ ዓይነት የጤፍ (ቀይ፣ ሰርገኛ፣ ነጭ)፣ እንዲሁም ጥራጥሬዎችን አቅርበናል” በማለት አብራርተዋል፡፡

የሸገር የከተማ ግብርና ህብረት ሥራ ማህበር ሊቀመንበር አክለው እንዳስረዱት፤ በአምራች እና በሸማች መካከል ያለው የገበያ ትስስር ከዓመት ዓመት ጥሩ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ትልቅ መሆን፣ አምራች እና ሸማች ተቀራርበው የሚወያዩበት እና ችግሮችን የሚፈቱበት መድረኮች መዘጋጀት፣ ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት እንዲሁም በዘርፉ ውጤታማ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ማህበራት፣ ኢንዱስትሪዎች እና ተቋማት ዕውቅና የመስጠት ልምድ መዳበሩ ያለው አበርክቶ ትልቅ ነው፡፡

“የግብርና ምርቶችን በጥራት፣ በብዛት እና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ በ2016 በጀት ዓመት ለነበረን አስተዋፅኦ ከተማ አስተዳደሩ ዕውቅናና ምስጋና ሰጥቶናል” ያሉት የሸገር ከተማ ግብርና ህብረት ሥራ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ኡካ ገመቹ፤ ይህም ለበለጠ ሥራ እንደሚያተጋቸው ጠቁመዋል፡፡ ጥራት ያለውን ምርት በብዛት፣ በዓይነትና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል፡፡ “በገበያ ማረጋጋቱ ላይ አቅማችን የፈቀደውን በጎ አሻራ እናሳርፋለን። እስካሁን ምርቶቻችንን ስናዳርስባቸው የነበሩትን ከአምስት ያልበለጡ የሸማች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች ቁጥር በመጨመር፤ በከተማዋ ላሉ አስራ አንዱም የሸማች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች ተደራሽ ለማድረግ አቅደን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡ የተለያዩ ምርቶችን በጥራት፣ በብዛት እና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ በከተማዋ ገበያ ላይ የበኩላችንን ሚና ለመወጣት እንጥራለን” በማለት የማህበራቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ኅብረት ስራ ኮሚሽን በመዲናዋ ያለው የግብይት እንቅስቃሴ የማረጋጋት ኃላፊነትን ከሚወጡ ተቋማት አንዱ ነው። ኮሚሽኑ ከተሰጡት ተግባርና ሃላፊነቶች መካከል፡- የሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት ከክልል አምራቾች ዩኒየን፣ ከኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር መልካም ቅንጅት በማጠናከርና የምርት ትስስር በማድረግ፤ የግብርና ምርቶችን፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን፣ የእንስሳት እና የእንስሳት ተዋፅፆ  የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋና ጥራት ለነዋሪው እና ለአባላት ለማቅረብ ሸማቹንና አምራቹን በማስተሳሰር ፍትሃዊና የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር ማድረግ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ይህንን ቁልፍ ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ኮሚሽኑ እየሠራ እና እያስገኘ ያለው ውጤት አበረታች ስለመሆኑ የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ልዕልቲ ግደይ ተናግረዋል፡፡

የመዲናዋን የሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት አቅም በማሳደግ የሸማቹን ህብረተሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በኮሚሽኑ ከተሠሩ እና እየተሠሩ ካሉ ተግባራት መካከል በአምራች እና በሸማች መካከል ጠንካራ የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉ እንደሆነ የጠቆሙት ኮሚሽነሯ፤ “ባለፈው 2016 በጀት ዓመት በተከናወነው ውይይት መድረክ እና በተፈጠረው የገበያ ትስስር አማካኝነት አበረታች ውጤት መጥቷል። በበጀት ዓመቱ ያልተቆራረጠ የምርት አቅርቦት፣ የተረጋጋ የግብይት ስርዓት፣ ያልተጋነነ የምርት መሸጫ ዋጋ እና በቂ የምርት ክምችት በሁሉም የሸማች ዩኒየኖቻች መጋዘን እንዲኖር ማድርግ ተችሏል። በዚህም መንግስት ካደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ነጋዴዎች ተፈጥሮ የነበረውን የምርት መደበቅ፣ አላስፈላጊ የምርት ዋጋ መጨመር… በተከሰተበት ወቅት እንኳን  የሸማች ዩኒየኖች፣ መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበራት በቂ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋና ጥራት በማቅረብ የምርት ዋጋ እንዳይንር ያደረጉት አሰተዋፆ ከፍተኛ ነበር” ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሃብተየስ ዲሮ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ በሰጡት መረጃ እንደጠቆሙት፤ በ2016 በጀት ዓመት በኮሚሽኑ አስተባባሪነት በተመቻቸ የገበያ ትስስር አማካኝነት 461 ሺህ 899 ኩንታል የግብርና ምርቶች፣ 279 ሺህ 535  ኩንታል የኢንዱስትሪ ምርቶች በድምሩ 741 ሺህ 434 ኩንታል ምርቶች ተገዝተው ወደ ከተማዋ ገብተዋል፡፡ ከእነዚህ ምርቶች መካከል፦ ጤፍ 309 ሺህ 499 ኩንታል፣ ጥሬ ስንዴ 19 ሺህ 500 ኩንታል፣ ገብስ 4 ሺህ 400 ኩንታል፣ ጥሬ በቆሎ 29 ሺህ 900 ኩንታል፣ ሽንኩርት 2 ሺህ 500 ኩንታል፣ ሩዝ 59 ሺህ 250 ኩንታል፣ መኮሮኒ 23 ሺህ 700 ኩንታል፣ ፓስታ 24 ሺህ 710 ካርቶን፣ የስንዴ ዱቄት 121 ሺህ 200 ኩንታል፣ የበቆሎ ዱቄት 22 ሺህ 200 ኩንታል ይገኙበታል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት በግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርት ትስስር ከተደረጉት ውስጥ የተሻለ ምርት ካቀረቡ አምራቾች መካከል፡- ሊባን የአምራች ገበሬዎች ዩኒየን (ጤፍ 8 ሺህ 600 ኩንታል)፣ ገመቹ ፉድ ኮምፕሌክስ (3 ሺህ 822 ኩንታል የስንዴ ዱቄት)፣ ስታር ኤ ትሬዲንግ (8 ሺህ 190 ካርቶን ፓስታ)፣ ላቫንቴ (ፈሳሽ ዘይት 352 ሺህ 314 ሊትር)፣ ሸገር ከተማ ግብርና ህብረት ስራ ማህበር (252 ኩንታል ጥራጥሬ) በዋናነት እንደሚገኙበት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሃብተየስ ዲሮ ጠቁመዋል፡፡ በተፈጠረው የአምራች ሸማች የገበያ ትስስርም በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት የሚቀርቡ ምርቶች በግል ነጋዴዎች ከሚቀርቡ ተመሳሳይ ምርቶች ጋር ሲነፃፀር ያለው የዋጋ ልዩነት ሰፊ ሆኖ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡ ለማሳያነትም፡- ጤፍ በኩንታል ከ1 ሺህ 500 እስከ 1 ሺህ 800 ብር፣ የስንዴ ዱቄት ከ1 ሺህ እስከ 1 ሺህ 200 ብር፣ ምስር ክክ እስከ 3 ሺህ ብር፣ አተር ክክ እስከ 1 ሺህ 5 መቶ ብር፣ መኮሮኒ ከ5 መቶ እስከ 550 ብር፣ ስጋ በኪሎ ከ3 መቶ ብር በላይ፣ ዘይት በሊትር ከ20 ብር በላይ ልዩነት ያለው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ የሸማች ህብረት ሥራ ዩኒየኖችን ከአምራቾች ጋር በገበያ ለማስተሳሰር ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረት ሥራ ኮሚሽን ባገኘነው መረጃ መሰረት በበጀት ዓመቱ የግብርና ምርት 505 ሺህ 251 ኩንታል፣ የኢንዱስትሪ ምርት 338 ሺህ 412 ኩንታል፣ ሌሎች 10 ሺህ 664 ኩንታል በአጠቃላይ 854 ሺህ 327 ኩንታል የሚሆን የምርት ግብይትን በቀጥታ  ለማስተሳሰር ዕቅድ ተይዟል፡፡ በዕቅዱ ከተያዘው ጥቅል የምርት መጠን ውስጥ፡- ጤፍ 324 ሺህ 974 ኩንታል፣ ጥራጥሬ 93 ሺህ 800 ኩንታል፣ በርበሬና ቅመማ ቅመም 1 ሺህ 820 ኩንታል፣ ቅቤና ማር 12 ኩንታል፣ በሬ በቁጥር 1 ሺህ 240፣ እንቁላል በቁጥር 4 ሚሊዮን 998 ሺህ 976፣ የስንዴ ዱቄት 130 ሺህ 896 ኩንታል፣ የበቆሎ ዱቄት 23 ሺህ 976 ኩንታል፣ ሩዝ 63 ሺህ 990 ኩንታል፣ መኮሮኒ 60 ሺህ 750 ኩንታል፣ ፓስታ 36 ሺህ 686 ካርቶን፣ ጥሬ በቆሎ 31 ሺህ 395 ኩንታል፣ ገብስ 4 ሺህ 752 ኩንታል፣ ፈሳሽ ዘይት 18 ሚሊዮን 332 ሺህ 659 ሊትር፣ ቡና 2 ሺህ 415 ኩንታል፣ ሽንኩርት 22 ሺህ 750 ኩንታል ይገኙበታል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት የሚከናወነውን የአምራች ሸማች ግብይት የተሳካ እና ውጤታማ ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የኅብረት ሥራ ኮሚሽን አስተባባሪነት ሕዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ የተከናወነው ይፋዊ የትስስር መድረክ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የንጋት በንፋስ ስልክ የሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ገብሬ ተክሌ፤ ከዚህ በፊት የተከናወኑ መሠል የገበያ ትስስር ተግባራት ያስገኙት ውጤት ምስክር መሆኑን አንስተዋል፡፡ እሳቸው የሚመሩት የሸማች ኅብረት ሥራ ዩኒየን የ2017 በጀት ዓመት የግብርና ምርቶችን ግዢ ለመፈፀም ቀደም ሲል ጀምሮ ዝግጅት እያደረገ ቆይቷል፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ህብረት ሥራ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የምርቶች መገኛ ወደሆኑት የአገሪቷ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ቅኝት እና ጥናት አድርገዋል፡፡ ከተወሰኑ ዩኒየኖች ጋርም ቀደም ብለው የገበያ ትስስር ማድረግ ችለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከአዳዲስ እና ቋሚ የግብርና ምርት አቅራቢ አምራች ዩኒየኖች እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ምርት አምራቾች እና አስመጪዎች ጋርም ሕጋዊ የገበያ ትስስር ፈፅመዋል። ይህንን ማድረጋቸው ህብረት ሥራ ዩኒየን በስሩ ላሉ 19 መሠረታዊ የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት፣ ከ58 ሺህ በላይ አባላት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠረው የክፍለ ከተማው ሸማች ማህበረሰብ ጥራት ያለውን ምርት፣ በብዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብና የማሰራጨት አቅምን ያሳድገዋል፡፡

ካለፉት ዓመታት ልምድ በመነሳት የ2017 በጀት አመት የአምራች ሸማች የቀጥታ የገበያ የትስስር ውጤታማ እንዲሆን በአምራቹም ሆነ በሸማቹ አካል ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ነጥቦች የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ልዕልቲ ግደይ አማካኝነት አፅንኦት ተሰጥቷቸው ተነስተዋል፡፡ እሳቸው በሰጡት ማሳሰቢያ መሰረት፤ ትስስር የፈፀሙ አካላት በትስስር ውላቸው ላይ ያሰፈሩትን ግዴታዎች ሁለቱም ወገኖች (አቅራቢ እና ሸማች) ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ አምራቾች ከገዢዎቻቸው (ከሸማቾቻቸው) ጋር ትስስር ለመፍጠር መተማመን የሚለውን መርህ እንደ አንድ ጉዳይ ማየት፣ የከተማ አስተዳደሩ የህብረት ሥራ ተቋም አመራሮችና ሠራተኞች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው፡፡ በውሉ መሰረት ግብይት መፈፀም፣ ለምርት ግዢ በቂ ፋይናንስ ማዘጋጀት፣ ምርት ግዢ ክፍያ በወቅቱ መፈፀም እንዲሁም ምርትን ፈጥኖ ማንሳት በከተማዋ ካሉ የሸማች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች በትኩረት እና በኃላፊነት ስሜት ሊተገብሯቸው ይገባል፡፡

በደረጀ ታደሰ


0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review