የአምራች ኢንዱስትሪውን የብልጽግና ተምሣሌት ለማድረግ የተያዙ ውጥኖች ውጤት እያስመዘገቡ ነው – የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

You are currently viewing የአምራች ኢንዱስትሪውን የብልጽግና ተምሣሌት ለማድረግ የተያዙ ውጥኖች ውጤት እያስመዘገቡ ነው – የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

AMN – መጋቢት 23/2017 ዓ.ም

የአምራች ኢንዱስትሪውን የብልጽግና ተምሣሌት ለማድረግ የተያዙ ውጥኖች ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በኢንዱስትሪ ልማት ይታዩ የነበሩ የመሬት፣ የግብዓትና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግሮችን በመቅረፍ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ወደ 61 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ለዘርፉ ይቀርብ የነበረውን የኃይል አቅርቦት ከ50 በመቶ በላይ ማሳደግ መቻሉንም በሰጡት ማብራሪያ አስታውቀዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ፣ የአምራች ዘርፉ ለሀገር ዕድገት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ ለብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፎች በተሰጠው ትኩረት የሀገሪቱን ዕድገት የሚያሳልጡ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገብ መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተቀመጠው ግብ ዘርፉ ተኪና ወጪ ምርቶችን በብዛትና በጥራት እንዲያመርት ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሀገር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቁመውመ፣ በ2014 የ 4 ነጥብ 8 በመቶ ፣ በ2015 የ 7 በመቶ ዕድገት እንዲሁም በ2016 የ10 ነጥብ 01 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡንም ገልጸዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት 12 ነጥብ 8 በመቶ የዕድገት ድርሻ እንደሚኖረው አመላክተው፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ የሕግና የአሠራር ሁኔታዎች መሻሻላቸው ለዕድገቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ አዲሱ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተወዳዳሪነትን የሚጨምር ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ትልቅ አበርክቶ እንዳለው እና ባለፉት አራት ዓመታት ከ 855 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡

በአስር አመቱ የልማት ግብ መጨረሻ በአነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር ግብ መቀመጡንም ገልጸዋል፡፡

የሀገርን ምርት ከመተካት አኳያም የተኪ ምርት ስትራቴጂን በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባት መቻሉን ጠቁመው፥ ሚኒስቴሩ በስትራቴጂው 96 ምርቶችን ለይቶ በአገር ውስጥ የመተካት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም የፀጥታ አካላት ደንብ ልብስን ጨምሮ ሌሎችንም ምርቶች ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉን መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በበጀት አመቱ ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ተኪ ምርቶችን በማምረት 2 ነጥብ 79 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማዳን መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review