የአረንጓዴ አሻራ፣ የኮሪደር ልማትና የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ስራዎች ለዜጎች ተስማሚ አካባቢ መፍጠር አስችለዋል-ሌሊሴ ነሜ (ኢ/ር)

AMN- ጥር 12/2017 ዓ.ም

የአረንጓዴ አሻራ፣ የኮሪደር ልማትና የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ስራዎች ለዜጎች ምቹና ተስማሚ አካባቢ መፍጠር ያስቻሉ መሆኑን የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሌሊሴ ነሜ ገለጹ።

ዋና ዳይሬክተሯ ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ብክለት ይብቃ፤ ውበት ይንቃ በሚል መሪ ሀሳብ ለስድስት ወራት የተካሄደው የአካባቢ ብክለት ቅነሳ ንቅናቄ ውጤታማ መሆኑን አንስተዋል።

የንቅናቄው መርሃ ግብር የዜጎችን በጤናማ አካባቢ የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብት ማስከበር፣ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ፣ የተፈጥሮ ሃብትን መጠበቅ ዓላማ አድርጎ የተካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም የተደረገው ንቅናቄ ስለ አካባቢ ጥበቃ፣ ስለ ብክለት ምንነት፤ የመከላከልና የማስወገጃ መንገዶች ላይ ግንዛቤ በመፍጠር የሚጠበቀውን ውጤት አስገኝቷል ብለዋል።

በንቅናቄው በየወሩ የፕላስቲክ፣ የአየር፣ የውሃ፣ የአፈር እና የድምፅ ብክለትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

በዚህም በሁሉም ክልሎች የተሻለ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ማስቻሉን አንስተው በስድስት ወራት ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በንቅናቄው በቀጥታ መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ያስጀመሯቸው የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የኮሪደር ልማት ለዜጎች ምቹና ለጤና ተስማሚ አካባቢን መፍጠር አስችለዋል ብለዋል።

የተለያየ አይነት የአካበቢ ብክለት ሲያጋጥም ለባለስለጣኑ ጥቆማ የሚሰጥበት የአሰራር ስርዓት ተግባራዊ መደረጉንም ኢንጅነር ሌሊሴ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ይህም የተጀመሩ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የላቀ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ”ብክለት ይብቃ ፤ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ሃሳብ ከሚያዚያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የብክለት መግቻ ንቅናቄ ማካሄዱ ይታወሳል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review