የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና በመቀነስ ረገድ ጉልህ አበርክቶ ያለው መሆኑ ተጠቆመ

You are currently viewing የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና በመቀነስ ረገድ ጉልህ አበርክቶ ያለው መሆኑ ተጠቆመ

AMN-ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ አጠናክራ የቀጠለችው የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና በመቀነስ እንዲሁም የውሀ ሀብትን በማሻሻል ረገድ ጉልህ አበርክቶ ያለው መሆኑ ተጠቆመ።

ዓለም አቀፍ የውሀ አጠቃቀምና የአየር ፀባይ (ሀይድሮሜት) ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ኮንፈረንሱን የከፈቱት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ፣በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ በሆነው የአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካ በተለይም ምስራቁ ክፍል የበዛ ዳፋ እያረፈበት ይገኛል ብለዋል። በዚህም የሀገራትንና የመንግስታትን ከንግግር ያለፈ ርምጃ ይሻልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከ 6 ዓመታት በፊት የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ሀገርን ፣ ቀጣናን ከፍ ሲልም ዓለምን ከቀውስ የማዳን የተግባር ርምጃ ነውም ብለውታል።

መርሀግብሩ እስካሁን ባለው ሂደትም በወረቀት ከሚጠቀስ በላይ የሚታይ ውጤት እያስገኘ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

መርሐግብሩ በኢትዮጵያ ያለውን የደን ሽፋን ወደ 23 በመቶ አሳድጓል፣ የከርሰ ምድር ውሀ ሀብት መጠንን አልቋል፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋዎችንም አስቀርቷልም ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

አላቂ የውሀ ሀብትን ለመጠበቅ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመመከትም በሀገራት መካከል ያለው የመረጃ ልውውጥ እንዲሁም የቅድመ አደጋ መከላከል ስርዓት ሊጎለብት እንደሚገባው ገልፀዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ፣ በየዓመቱ ከ 20 ሚሊየን በላይ ዜጎች በሚሳተፉበት የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር እስካሁን ባለው ሂደት ከ40 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለው የአየር ንብረት ለውጥን እየገቱ ይገኛሉ ብለዋል።

ከነዚህም ችግኞች ውስጥም ሩቦቹ በአባይ ወንዝ ተፋሰስ የተተከሉ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ ይህም የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ዘላቂ የውሀ ሀብትን በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ድርሻ እየተወጣ ስለመሆኑ ማሳያ አድርገዋል።

የዓለም ሜትሮዎሎጂ ድርጅት ፕሬዚዳንት አብዱላ አህመድ አልማንዱስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዓለማችን እጅግ ሞቃቱንና ፈታኝ የከባቢ አየር ጠባይ እያሳለፈች ስለመሆኗ አንስተዋል።

2023 በግማሽ ምዕተዓመት ውስጥ ሞቃታማው ዓመት ነበር ያሉት ፕሬዚዳንቱ መንግስታት ከወዲሁ በተፈጥሮና ውሀ ሀብት ጥበቃ ረገድ አፋጣኝና ዘላቂ መፍትሄ ካላበጁ በቀር መጪው ጊዜ አሁን ካለው የባሰ አስከፊ የመሆን ዕድል አለውም ብለዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከውሀ ሀብት አጠባበቅ፣ ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ አንፃር ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ርምጃ እየወሰደች ስለመሆኗም ገልፀዋል።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ ተጀምሮ ተጠናክሮ የቀጠለው የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የአየር ንብረት ለውጥን በመግታት ዘላቂና የውሀ ሀብትን በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አብርክቶ ያለው ነውም ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

በኢፌዴሪ የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተዘጋጀው የመጀመሪያው የሀይድሮሜት ኮንፈረንስ እስከነገ የሚቀጥል ይሆናል።

በአቡ ቻሌ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review