የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር የትውልድ ግንባታ ስራ አካል ነው :- የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሰራተኞች

You are currently viewing የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር የትውልድ ግንባታ ስራ አካል ነው :- የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሰራተኞች

AMN- ሀምሌ 4/2016 ዓ.ም

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር የትውልድ ግንባታ ስራ አካል መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሰራተኞች ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሠራተኞች ጋር በመሆን አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

በመርሃ-ግብሩም ከሐረር እና ከኮንሶ አካባቢዎች የመጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች በጫካ ፕሮጀክት ባከናወኑት የሀገር በቀል የእርከን ሥራ ላይ ችግኝ የመትከል መርሃ-ግብር ተከናውኗል፡፡

በዚህም ከዚህ ቀደም የነበሩ የባህር ዛፍ ተክሎችን በሀገር በቀል ችግኞች የመተካት ሥራ ተከናውኗል፡፡

በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ የጽህፈት ቤቱ ሰራተኞች፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከስነ ምህዳርና አካባቢ ጥበቃ ባሻገር ለመጪው ትውልድ የተሻለ ሀገር ማስረከብ የሚያስችል የትውልድ ግንባታ ስራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ቀነዓ ያደታ(ዶ/ር)፤ መርሃ ግብሩ ከዛሬ ባሻገር ነገን አሻግሮ የተመለከተ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም የማህበረሰቡን የአረንጓዴ ባህል የቀየረና ዜጎችን ለአንድ ዓላማ በጋራ ያሰለፈ መርሃ ግብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሴቶች ማህበራዊና አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ዳንኤል በበኩላቸው፤ መርሃ ግብሩ ከኢትዮጵያ ባለፈ በቀጠናው የሚያጋጥመውን የአየር ጠባይ ለውጥ ለመቋቋም ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአንድነት ፓርክ ሰራተኛ የሆኑት ፍጹም ዓለማየሁ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ከሀገር በቀል የአፈር ጥበቃ እውቀት ጋር በማስተሳሰር ለመተግበር እየተከናወነ ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ችግኝ ከመትከል ባለፈ በመንከባከብ ስራ ላይ በስፋት ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ የቤተ መንግስት አስተዳደር ሰራተኛ የሆኑት ግሩም ዘውዱ፤ ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ስራን ዘወትር ባህል አድርጎ ማከናወን እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

#Addisababa

#Ethiopia

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review