በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በ2011 ዓ.ም ተጀመረ፡፡ ተግባራዊ መሪ እና መሪውን የሚከተል ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብሩን በስኬት ተወጣችው፡፡ በዚሁ ሥራም ዓለምን አስደመመች፡፡
ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደው የመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ኢትዮጵያ ተከለች፡፡ይህም በወቅቱ በሕንድ የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ ሥራ በ12 ሰዓታት 66 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረወስን እንድትሰብር አስችሏታል፡፡
እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ ለአራት ዓመታት በተካሄደው የመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብር 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 25 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ ከማመንጨት ጀምሮ ችግኝ በመትከል እና በመንከባከብ በየቀኑ ለሚመሩት ህዝብና ሀገር አርአያነታቸውን በተግባር አሳይተዋል፡፡
ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በ2015 ዓ.ም 25 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል በማቀድ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡
በ2016 ዓ.ም ለስድስተኛ ጊዜ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከ615 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እስካሁን ድረስ 40 ቢሊዮን ችግኞችን ተክላለች፡፡
በዘንድሮ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል አቅዳለች፡፡ ከነዚህም መካከል 50 በመቶ የሚሆነው ለምግብነት፣ ለመድሐኒትነትና የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እንዲሁም ለውበትና ለአከባቢ ጥበቃ የሚውሉ ናቸው፡፡
የተየዘው እቅድ እንደሚሳካ አያጠራጥርም፡፡ በተግባር የሚያሳይ መሪ እና ከመሪው ጋር የሚተጋ ህዝብ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ዓለምን እያስደነቀች ትቀጥላለች፡፡
ከሰሞኑ የተካሄደው የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ ጉባኤ ላይ ባለ ራዕዩ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የፓርቲው ፕሬዝዳንት በመሆን በከፍተኛ ድምጽ ተመርጠዋል፡፡
ኢትዮጵያም ከልብ በሚያገለግሏት መሪዎች እየተመራች በጀመረችው አስደማሚ ለውጧ ጉዟዋን ትቀጥላለች፡፡
በማሬ ቃጦ