የአብሮነታችን  መሠረቶች

ኢትዮጵያውያን ሽማግሌ ካለ ምክር አይጠፋም፡፡ የተጠቃ አቤት ይላል፤ ሽማግሌ ይገላግላል፡፡ ሽማግሌን ከምክር ከመለየት፣ ከምግብ መለየት፡፡ ሽማግሌ ካለበት ነገር አይሰረቅ፡፡ ጎበዝ ካለበት በትር አይነጠቅ፡፡ ሽማግሌ በምክሩ አርበኛ በሰናድሩ… የሚሉ በርካታ ምሳሌያዊ ንግግሮች አሉን፡፡ እነዚህ አባባሎች የተነገሩት ለአንድ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ማህበረሰቡ በእድሜ የገፉ ሽማግሌዎችን ምክርና ሃሳብ እንደሚሰማ፣ እነሱም በዓመታት የኑሮ ልምዳቸው ብልህ፣ አስተዋይና ፍትህ አዋቂ መሆናቸውን ነው፡፡ በዚህም የብሄር ብሔረሰቦች ሀገር በሆነችው  ኢትዮጵያ አብሮነትን ለማጽናት እና ሰላምን ለማስፈን የባህላዊ ሽምግልና ስርዓቶች ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም ከነገ በስቲያ ማለትም ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም “ኀብራችን ለሰላማችን” በሚል የሚከበረውን “የህብር ቀን” መነሻ በማድረግ በሀገራችን ውስጥ ከሚገኙና ሰላምን ለማረጋገጥ፣ ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን ለማጽናት ትልቅ ድርሻ ከሚወጡ ባህላዊ የሽምግልና ስርዓቶች ውስጥ የተወሰኑትን በአጭሩ አሰናድቷል፡፡

አፊኒ        

በሃላባ የኦጋቴ ስነ ስርዓት ከፊል ገጽታ

ባለፈው ዓመት በአራርሶ  ገረመው (ዶ/ር) የተጻፈና  ትኩረቱን  በሲዳማ  የሰላም  ዕሴት ዙሪያ ያደረገ አንድ መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል፡፡ የመጽሐፉ ርእስ “አፊኒ“ የተሰኘ ሲሆን ትርጉሙም “አልሰማችሁም  ወይ?” የሚል ነው፡፡ መጽሐፉ የልዩነት ሀሳብ ያላቸው ሰዎች መሰማት እና መደማመጥ ይኖርባቸዋል የሚል ሀሳብን በውስጡ ይዟል፡፡ ከዚህም ባለፈ “አፊኒ” የተሰኘ ፊልም ተሰርቶ መመረቁ የሚታወስ ነው፡፡ እነዚህ የጥበብ ስራዎች መነሻ ያደረጉት  “አፊኒ” የተሰኘውን የሲዳማ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት ነው፡፡

የሲዳማ ህዝብ  ለዘመናት ጠብቆና ከትውልድ ወደ ትውልድ አሸጋግሮ ያቆየው የራሱ የሆነ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ አለው። ከዚህ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ውስጥ “አፊኒ” ዋነኛው ነው።

“አፊኒ” ጉዳዩ የሚመለከታቸው ግለሰቦች ወይም አካሎች በሸንጎ ውስጥ በውይይት ወይም በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት እንዲሳተፉ ዕድል የሚሰጥበት መንገድ ነው። ሀሳብን ለማንሸራሸርና ለማሰባሰብ ጊዜ ለማግኘት ጭምር የሚረዳ የንግግር መሳሪያም ነው፡፡ ሽማግሌዎቹ “ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ” እያሉ በአባባሎች እያዋዙ ግራ ቀኙን ያደምጣሉ፡፡

“አፊኒ” የቀረበውን ሀሳብ አቅጣጫ ተረድቶ እየተከታተለ ያለው ወገን እንዲረዳውና ሀሳቡን ለተሰብሳቢው ያደረሰው ወገን ጊዜ ወስዶ በማጤን እውነትን በመግለጥ ሙግቱን ለመርታት ወሳኝ የሆኑ ቁልፍ መከራከሪያ ምክንያቶችን ማሰባሰቢያ ነው። እንዲሁም የሀሳቡ ደጋፊዎች ጉዳዩን በአፅንኦት እንዲከታተሉ እና ደጋፊ ሀሳብ እንዲያመነጩ ለማጠናከር ጭምር ያገለግላል። ይህም ለመጨረሻ ውሳኔ አቅጣጫ ደጋፊዎቹን ለማስማማት ያለመ ነው። የሚቃወም ካለም “እዚህ ጋር የተለየ ሀሳብ አለኝ” ብሎ የመቃወሚያ ሀሳቡን እንዲያቀርብ  የአፊኒ ስርዓት ዕድሉን እንደሚሰጥ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በመሬት፣ በድንበር፣ በትዳር፣ ነፍስ በማጥፋት፣ በጠለፋ፣ የሰው ሀቅ በመብላት፣… ስሞታ የቀረበባቸው ጉዳዮች ወደ ሕግ ከማምራታቸው በፊት በሲዳማ ባህል በአፊኒ ስርዓት ይዳኛሉ። በማኅበረሰቡ ዘንድ ግጭቶች በአፊኒ የመፈታት እድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ይህ ስርዓትም ህብረ ብሄራዊ በሆነችው ኢትዮጵያ ተከባብሮ፣ ተሳስቦና ተረዳድቶ በሰላም ለመኖር ያለው ሚና ከፍ ያለ ነው፡፡ የሲዳማ እርቅን፣ ሰላምንና ይቅርባይነትን እያሰፈነ ለዘመናት የኖረው ድንቅ ባህላዊ እሴት “አፊኒ” በሀገር አቀፍ ደረጃ ለኪነ ጥበብ መነሻ ሃሳብ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡

የቢያ ግጭት አፈታት

የቡርጂ ሽማግሌዎች አብሮነትንና ሰላምን ለማፅናት የቢያ አስተዳደር ድርሻው የጎላ ነው

የቡርጂ ማህበረሰብ  የራሱ የሆነ ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ እና የአኗኗር ዘይቤ ያለው ሕዝብ ነው። ማህበረሰቡ አብሮነትን ለመገንባት፣ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር፣ ሰላምን ለማስፈን፣ ፍቅርን ለማጽናት  የሚያስችሉ በሀገር በቀል እሴቶች የዳበረ ባህልና ማንነት አለው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የቢያ ግጭት አፈታት ነው፡፡ “ቢያ” የሚባለዉ በቡርጂ የአስተዳደር መዋቅር የራሱ የሆነ መልክዓ ምድራዊ ክልል ያለዉ ሲሆን፤ የራሱ የሆነ ባህላዊ ማኅበራዊ አስተዳደር አለው። ስለሆነም በማህበረሰቡ ውስጥ የሚከሰቱትን ቅራኔዎችና አለመግባባቶች የሚፈታባቸዉ ዘዴዎች አሉት፡፡ የቢያ አስተዳደር በአንድ መሪ የሚመራ የሽማግሌዎች አስተዳደር አለዉ፡፡ ይህም አስተዳደር ህዝቡ በማንኛዉም ደረጃ የሚከሰተውን ግጭት እና አለመግባባት መፍትሔ የሚፈልግበት አካል ነዉ፡፡

ስለሆነም ግጭት በሚከሰትበት ወቅት በበዳይ እና በተበዳይ መካከል የተከሰተዉን ግጭት በሀገር ደንብና ሥርዓት መሠረት መፍትሔ እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡ እንደ አካባቢዉ ስፋት ብዛት ያላቸውን ሰፈሮች ያቅፋል፡፡ ስለሆነም ሰፈሮች በመካከላቸው የተከሰተውን ግጭት በእርቅ ለመፍታት ካልቻሉ የቢያ ጉባኤ ጉዳዩ ሲቀርብለት አይቶ መፍትሔ እንዲፈልግለት ይደረጋል፡፡

ኦጋቴ

የሲዳማ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት አፊኒ በከፊል

ኢትዮጵያ ካሏት በርካታ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች መካከል የሀላባ ብሄረሰብ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ እና ባሕላዊ ሸንጐ ወይም “ኦጋቴ” አንዱ ነው። “ኦጋቴ” የሀላባ ብሄረሰብ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች መፍቻ ስርዓት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ በትልቅ ዋርካ ጥላ ስር የሚካሄድ የሀላባ ብሔረሰብ ባሕላዊ ሸንጐ ነው።

ባሕላዊ ሸንጐው በተወሰነ ጊዜ ወይም አስቸኳይ ሁኔታ ካጋጠመ ከመደበኛ ጊዜ ውጭ እየተሰበሰቡ ስለብሄረሰቡ አጠቃላይ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ውሳኔ የሚተላለፍበት ባህላዊ ተቋም ነው።

የዕለቱ የሸንጐ ስርዓት የሚጀምረው ሶላት ተሰግዶና ቡና ቀርቦ ከተጠጣና ምርቃት (ዱአ) ከተደረገ በኋላ ሲሆን፤ ወደ ዝርዝር ጉዳዩ ለመግባት በሁለቱ “ቆርቶዎች” አማካይነት የእለቱ አጀንዳዎችና አዳዲስ ጉዳዮችም ካሉ ይፋ ይደረጋሉ።

የሀላባ ቁሊቶ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት እ.ኤ.አ. በ2022 “የሀላባ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት – ኦጋቴ” በሚል ርእስ በይፋዊ ገጸ-ድሩ ይፋ ባደረገው መረጃ ላይ እንደገለጸው “ቆርቶዎች” በሀላባ ብሄረሰብ የኦጋቴ ስርዓት ላይ ከሳሽንም ሆነ ተከሳሽን በመወከል የሚከራከሩ ሰዎች ናቸው፡፡

በዋናዎቹ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ከመደረጉ በፊት ዜና “ዱዱቦ” ያለው እንዲያቀርብ ይጠየቃል። በዜናው የሀገር ውስጥ ጉዳዮች፣ የአጐራባች ብሔረሰቦችና በየአካባቢው የተፈጠሩ ጉዳዮች ካሉ ይካተታሉ። ከሸንጐው አባላት መካከልም ሳይቀርብ ቀርቷል ብለው ያሰቡትን ዜና የማቅረብ መብታቸው ይጠበቃል።

ከዚህ በኋላ ሀገር ሰላም መሆኑ ተረጋግጦ በብሔረሰቡ አባባል “አዞሃ ወገሬት” (የወተት ሰላም እንደማለት ነው) ከተባለ በኋላ ነው ወደ አጀንዳዎቹ ውይይት የሚገባው። ውይይቱ በሁለቱ ቆርቶዎች እየተመራ ከክርክርና ስምምነት ደረጃ የሚደረሰው ተሰብሳቢዎች በአንደኛው ቆርቶ ሀሳብ ላይ የተቃውሞ ወይም የድጋፍ አስተያየት ካቀረቡ በኋላ ነው። ይህም “ጉምጉማ” ይባላል። ማህበረሰቡም በዚህ ስርዓት አብሮነትን እያጸና ሰላምን እያሰፈነ ዘመናትን የተሻገረ ሲሆን፤ ዛሬም ለሀገር ሰላምና እድገት የበኩሉን እያበረከተ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ  የተወሰኑትን ብቻ ጠቀስን እንጂ ኢትዮጵያ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ባህላዊ የግጭት አፈታት መንገዶች፣ የሽምግልና ስርዓቶች፣ ወጎች፣ ማንነቶችና ትውፊቶች ያሏት ሀገር ናት፡፡ እነዚህን ውድ ሀብቶች ህብራዊነትን ለማጠናከር፣ አብሮነትንና ሰላምን ለማጽናት ልንጠቀምቸው ይገባል፡፡ በተጨማሪም ልክ እንደ አፊኒ ስርዓት ሁሉ ሌሎችንም በመጽሐፍ፣ በፊልም፣ በዘፈንና በሌሎችም የጥበብ መንገዶች ማስተዋወቅና ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review