የአቶ ቡልቻ ደመቅሳ አጭር የህይወት ታሪክ

AMN – ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በምእራብ ወለጋ ዞን በቦጂ ድርመጂ ወረዳ ከአባታቸው አቶ ደመቅሳ ሰንበቶ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ናሲሴ ሰርዳ በ1922 ዓ.ም ነው የተወለዱት፡፡

ለቤተሰቡ 4ኛ ልጅ እና ብቸኛ ወንድ ልጅ የሆኑት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በጊንቢ አድቬንቲስት እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኩየራ አድቬንቲስት ተምረዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርታቸውንም አራት ኪሎ ዩንቨርሲቲ በመግባት የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በመከታተል በከፍተኛ ውጤት ተመርቀዋል፡፡

በዩንቨርስቲው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ከተመረቁ 10 ተማሪዎች መካከል አንዱ በመሆንም ወደ አሜሪካ በመሄድ በሲራኪዩዝ ዩንቨርሲቲ ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በመምህርነት አገልግለዋል፡፡

በቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስትም በገንዘብ ሚኒስቴር በበጀት ዳሬክተር እንዲሁም ምክትል የገንዘብ ሚኒስትር በመሆንም አገልግለዋል፡፡

የደርግ መንግስት ስልጣን ላይ ሊወጣ አከባቢ የገንዘብ ሚንስቴር መስሪያ ቤትን ለቀው ወደ ሀገረ አሜሪካ አቅንተዋል፡፡

በዚያም ሳሉ በዩ ኤን ዲ ፒ እንዲሁም በዓለም ባንክ 20 አፍሪካ ሀገራትን ወክለው ሰርተዋል፡፡

የደርግ መንግስት መውደቅን ተከትሎ ከ17 ዓመታት የውጭ ሀገር ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በምጣኔ ሀብት አበርክቷቸው አዋሽ ባንክ እንዲቋቋም እና እሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የባንኩ መስራች እና ፕሬዚዳንት በመሆን ረዘም ላለ ጊዜ ያለ ክፍያ ሰርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እንዲስፋፋ በፖለቲካው ዓለም ተሰማርተው የራሳቸውን አስተዋጽኦም አበርክተዋል፡፡

እንዲሁም በኦሮሞ ኮንግረስ ፓርቲ ውስጥ በመሳተፍ እና በምርጫ በመወዳደር አሸንፈው ፓርላማ በመግባት ሀሳባቸውን በነፃነት በመሰንዘር ይታወቃሉ፡፡

ሀገርን መውደድ፣ ማንነትን ማክበር፣ ሀቀኝነት፣ ሰው ወዳድነት እና ሩህሩህነት የእርሳቸው መገለጫዎች ናቸው፡፡

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ባለ ትዳር እና የስድስት ልጆች አባት ሲሆኑ አስራ አንድ የልጅ ልጅ ለማየትም በቅተዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review