AMN – ታኀሣሥ 21/2017 ዓ.ም
የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም ለማሳደግና የገበያ ትስስርን ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት አስታውቋል፡፡
“የእኛን ምርት ለእኛ” በሚል መሪ ሃሳብ ከታህሳስ 20 እስከ ታህሳስ 27 የሚቆይ ኤግዚቢሽንና ባዛር በአዲስ አበባ ተከፍቷል።
በሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ ትኩረት ባደረገው በዚህ ባዛርና ኤግዚቢሽን ከሀገሪቱ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የተለያዩ ኢንተርፕራይዞች ተሳታፊ ሆነዋል።
በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች ተገቢውን ድጋፍ አግኝተው ምርቶቻቸውን በጥራት እንዲያመርቱ በተሰሩ ስራዎች ለውጦች መታየታቸውን የገለፁት የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ (ዶ/ር) በዚህም ዘርፉን ማሳደግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታና ሌሎች መመሪያዎችን በማዘጋጀት ወደ ተግባር እየተቀየሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም የገጠር ኢንደስትሪያላይዜሽን ፕሮግራም በማዘጋጀት የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በማቋቋም የየአካባቢውን አቅም ለመጠቀምና የስራ ዕድልን ለመፍጠር የሚያስችሉ ስራዎች እየተተገበሩ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ ቅንጅታዊ ስራዎች በዘርፉ ተጠናክረው መቀጠላቸውን አንስተው ኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪ ለማድረግ የገበያ ትስስሮች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከታህሳስ 20 እስከ ታህሳስ 27 የሚቆየው ኤግዚቢሽንና ባዛር ምርቶችን ከማስተዋወቁ ባሻገር ከአጋር አካላት ጋር በጋራ ለመስራት ያስችላል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በዚህ ባዛርም ከሀገሪቱ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ኢንተርፕራይዞች እንዲሳተፉ መደረጉንም ገልፀዋል።
በራሄል አበበ