የአንካራው ስምምነት እንዲተገበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

You are currently viewing የአንካራው ስምምነት እንዲተገበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

AMN – ታኅሣሥ 19/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በአንካራ ያደረጉት ስምምነት እንዲተገበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አንጋፋው ዲፕሎማትና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡

የአንካራው ስምምነት ውጤታማ የሆነ የሰላም እርምጃ መሆኑን አምባሳደሩ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ከራሳቸው ብሄራዊ ጥቅም በመነሳት ስምምነቱ የማያስደስታቸው አካላት እንዳሉ ይታወቃል ያሉት አምባሳደር ዲና እነዚህ ወገኖች ስምምነቱ ገና ከጅምሩ እንዲደናቀፍ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ስምምነቱን መተግበር ላይ ከሁሉም አካላት ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

“ከግል ጥቅም በመነሳት የሚጣረሱ ሀሳቦችን የሚሰጡ አካላት አሉ” ያሉት አምባሳደር ዲና ነገር ግን ጥቃቅን ነገሮችን ንቆ በማለፍ ለትልቁ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ለስምምነቱ ስኬት እና ውጤታማነት አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ ከሁሉም ወገኖች ይጠበቃልም ብለዋል፡፡

ስምምነቱን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ አካላት መኖራቸውን መገንዘብ በራሱ ትልቅ ነገር ነው ያሉት አምባሳደሩ በተለይም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ስምምነቱን ለማደናቀፍ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች እንዳይሳኩ አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ከስምምነቱ ባለቤቶች በኩል የሚደረጉ ጥረቶች ለስምምነቱ ስኬት የላቀ ድርሻ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቀይ ባህር አዋሳኝ አካባቢ መኖሯ እና ታሪካዊም ሆነ መልክዐምድራዊ የቀይ ባህር ተጠቃሚነት እንዳላት እየታወቀ አንዳንድ አካላት ኢትዮጵያ ከባህሩ ተጠቃሚነት እንድትርቅ የሚጠቁሙ መልዕክቶችን ማስተላለፋቸው አዲስ ነገር አለመሆኑንም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያን የባህር በር ፍላጎት ከሶማሊያ ሉዓላዊነት ጋር ማያያዙም ተመሳሳይ የአግላይነት አካሄድ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን ታሪካዊ ጠላቶች የሚሉትን ሳይሆን ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የጋራ ተጠቃሚነታቸውን በማስቀደም መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም በምንም የሚተካ አይደለም ያሉት አምባሳደር ዲና በዚህ ዙሪያ ዜጎች በፍጹም አንድነት እና መደማመጥ መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል፡፡

በሃብታሙ ሙለታ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review