ዛፎች የከተሞች ሳንባና የልብ ምት ማዕከል ናቸው። ዛሬ በዓለም ላይ የሚገኙ ትላልቅ ከተሞች በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ እያጋጠማቸው ያለውን ከፍተኛ ሙቀትና የጎርፍ አደጋ ለመከላከል፣ የሰዎችን ጤና ለመጠበቅ ለችግኝ ተከላ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ መዲና፣ የአፍሪካ ህብረት እና የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባም ለችግኝ ተከላ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሰራች ትገኛለች፡፡ መዲናዋ ባለፉት አምስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ከ58 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ተክላለች፡፡ የከተማዋ አረንጓዴ ሽፋንም በ2008 ዓ.ም 2 ነጥብ 8 በመቶ ከነበረው አሁን ላይ 17 በመቶ ደርሷል፡፡
የአዲስ አበባ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ይመኙሻል ታደሰ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እንዳብራሩት፣ በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በተያዘው የክረምት ወራት በአዲስ አበባ ከ20 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ግዜ ድረስ 15 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ሲነሳም በአንድ ጀንበር በርካታ ሰዎች የሚሳተፉበትና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች የሚተከሉበት የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ መርሃ ግብር ባለፉት ዓመታት በአንድ ቀን በርካታ ችግኞችን በመትከል እንደ ሀገር የዓለምን ክብረወሰን መስበር ተችሏል። በዘንድሮው ዓመትም 600 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል፡፡
አዲስ አበባ ከተማም ከዚህ ቀደም በነበሩ የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች ከያዘችው ዕቅድ በላይ ተክላለች፡፡ ለአብነትም በ2015/16 የችግኝ ተከላ በአንድ ጀንበር ለመትከል ታቅዶ ከነበረው ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ በማሳካት ከዕቅድ በላይ መከወን ተችሏል፡፡ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ደግሞ በአንድ ጀንበር 6 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ነው፡፡ ለዚህም በከተማዋ በሚገኙ 11 የችግኝ ጣቢያዎችና በጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል የፈሉ ችግኞች ተከላ ወደሚከናወንባቸው አካባቢዎች እየተጓጓዙ እንደሚገኝ ወይዘሮ ይመኙሻል ተናግረዋል፡፡
የችግኝ ተከላ የሚከናወንባቸው አስራ ሁለት ቦታዎችም ተለይተዋል፡፡ ለችግኝ ተከላውም ጉድጓዶችን ከማዘጋጀት ጀምሮ እስከ ተከላ ባለው ስራ የከተማዋ ነዋሪዎች በስፋት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያውና በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል የሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክተር አቶ መክብብ ማሞ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ ያለንበት ወቅት የነሀሴ ወር እንደመሆኑ መጠን በርካታ አካባቢዎች የተቆፈሩ ጉድጓዶች በውሃ ይሞላሉ፡፡ ህብረተሰቡ ለተከላ እስከወጣ ድረስ ጉድጓድ ውስጥ ውሃ እያለ ችግኝ መትከል፣ ችግኞቹ እንዳይፀድቁ ስለሚያደርግ በጉድጓድ ውስጥ ያለውን ውሃ ማጠንፈፍ፣ ጉድጓዱን የሚያዘጋጁ አካላት በዙሪያው በቂ አፈር እንዲኖር ማድረግ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም አፈር ቀድሞ ተዘጋጅቶ ከሆነ ቀድሞ በዝናብ ታጥቦ አብዛኞቹ ቦታዎች ላይ ይሄዳል፡፡ ለዚህም ጉድጓዱን በበቂ ሁኔታ መሙላት የሚያስችል አፈር ማዘጋጀት፣ ተከላውም ሲከናወን ችግኙ በጣም ወደ ውስጥ እንዲገባ ከተደረገና ግንዱን አፈር ከነካው ስለሚበሰብስ ችግኙ ላይ አብሮ በመጣው አፈር ልክ ተከላውን ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡
የችግኝ ተከላው ከዘር ዝግጅት፣ ችግኝ ማባዛት እስከ መንከባከብ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበትና በርካታ ወጪ የወጣበት ስለሆነ ውጤታማ በሆነ መንገድ መትከል ያስፈልጋል፡፡ ህብረተሰቡ ችግኝ ለመትከል ሲወጣ ‘ይኼ የእኔ ኃላፊነት ነው፤ የዜግነት ድርሻዬን ነው የምወጣው’ በማለት መሳተፍ አለበት፡፡ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በእንክብካቤ ስራው ላይም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚገባው አቶ መክብብ ተናግረዋል፡፡
በችግኝ አተካከል ላይ የህብረተሰቡ ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም፣ በተከላ ወቅት ተሳታፊዎች የተከላው ቦታ ላይ እንደደረሱ ችግኝ ከማንሳታቸው በፊት፣ እንዴት መትከል እንዳለባቸው በቂ ገለፃ ከተሰጣቸው የችግኞችን የፅድቀት መጠን ለማሻሻል ያግዛል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
በተለይ በጫካ ወይም ሳር ውስጥ የችግኝ ተከላ ሲከናወን ዙሪያውን ሳሩን በደንብ ማፅዳት ያስፈልጋል፡፡ ቀጣይም እንክብካቤው ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል እንደ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን፣ ፍትህ ሚኒስቴር፣ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ያሉ ተቋማት ሮቶ ጭምር በማቅረብ የተከሉትን ችግኝ በመንከባከብና በማፅደቅ ውጤታማ ከሆኑት ይጠቀሳሉ፡፡ ሌሎች ተቋማትም የእነዚህን አርዓያነት በመከተል ከመትከል ባሻገር የፅድቀት መጠን እንዲጨምር በመስራት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አቶ መክብብ ተናግረዋል፡፡
በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ችግኝ ለተከላ ተዘጋጅቷል፡፡ ለአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላም በማዕከሉ የፈሉ ችግኞች ወደ ለሚ ኩራ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ አቃቂ ቃሊቲና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች ተከላ በሚከናወንባቸው ቦታዎች እየተጓጓዙ እንደሆነ አቶ መክብብ ገልፀዋል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ