AMN – መጋቢት 3/2017 ዓ.ም
የአንጋፋው የማሲንቆ እና በገና ተጫዋች አለማየሁ ፋንታ አስከሬን ለብዙ አስርት ዓመታት ባስተማሩበት ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ሽኝት እየተካሄደ ነው።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በተወካያቸው አማካኝነት የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።
በ1927 ዓ.ም በወሎ አካባቢ የተወለዱት አንጋፋው የማሲንቆ እና በገና ተጫዋች፣ ድምጻዊ እና የሙዚቃ መምህር አለማየሁ ፋንታ በተወለዱ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል::
አለማየሁ ፋንታ የግጥምና ዜማ ድርሰት፣ ክራር፣ ማሲንቆ እና በገና በመጫወት ይታወቃሉ።
ያላቸውን ጥልቅ ተሰጥዖ እና እውቀትም ለትውልድ በማካፈል ለበርካታ አሥርት ዓመታት በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግለዋል፡፡
በተለየ የማሲንቆ አጨዋወታቸው የሚታወቁት አለማየሁ ፋንታ፣ በዓለም ዙሪያ የኢትዮጵያን ባህል ማስተዋወቅ የቻሉ ናቸዉ፡፡
በዚህም የባህል አምባሳደር የሚል ማዕረግ እንዳገኙ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
ባከናወኑት ተግባር ከዓለም አቀፍና ከሀገር ውስጥም የተለያዩ ሽልማቶችን ያገኙ ነበር።
የባህል አምባሳደር አርቲስት እና የሙዚቃ መምህር አለማየሁ ፋንታ ለ60 ዓመታት በዘለቀ የትዳር ህይወታቸው 3 ወንዶች እና 3 ሴቶች ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፣ የልጅ ልጅም ማየት የቻሉ ናቸው።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦች የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።
የአስክሬን ሽኝት መርሐ-ግብሩ እንደተጠናቀቀ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት በገነተ ፅጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው እንደሚፈጸም ተመላክቷል፡፡
በሄለን ጀምበሬ