AMN- ጥር 1/2017 ዓ.ም
የጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1362/2017 በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት መጽደቁ ይታወሳል።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ አዋጁን በተመለከተ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
አዋጁ በጤናው ዘርፍ በተበታተነ እና ለአፈፃፀም ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ የሚገኙ የጤና አገልግሎቶችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በአንድ ማእቀፍ ሕግ እንዲወጣ አስፈላጊነቱ እንደታመነበት ገልጸዋል።
ከእነዚሁ ድንጋጌዎች በተጨማሪም አሁን ወቅቱ ከደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ የተጣጣመ አዳዲስ የጤና አገልግሎት ለመዘርጋት፣ የማህበረሰቡን ባህልና ሃይማኖትን፣ ነባር ህጎችን በጥንቃቄና በጥልቀት በመመልከት እንዲሁም በስራ ላይ የነበሩ ድንጋጌዎችን በማሻሻል ወጥ የሆነና ለአፈፃፀም ግልፅ የሆነ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑ ተመላክቷል።
የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ፍላጎት፣ መብትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ፍትሃዊ፣ ጥራቱ የተጠበቀና ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን ሙያዊ መብትንም ያካተተ አዋጅ መሆኑን ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡
የአዋጁ መጽደቅ በሀገራችን የሚሰጠውን የእናቶች እና ህጻናት ጤና አገልግሎት ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።