AMN – መጋቢት 3/2017 ዓ.ም
ለምሽቱ ሶስት ሰዓት ሩብ ጉዳይ የሚጀመረው የፈረንሳዩ ሊል እና የጀርመኑ ቦርሲያ ዶርትሙንድ ጨዋታ የዛሬ መክፈቻ ነው፡፡
ሁለቱ ክለቦች ባለፈው ሳምንት በሲግናል ኢዱና ፓርክ ተጫውተው 1ለ1 መለያየታቸው ይታወሳል፡፡
ከምሽቱ አምስት ሰዓት ሲል ሶስት ጨዋታዎች በአውሮፓ የተለያዩ ከተሞች የሚጀመሩ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከል ሁለቱ የማድሪድ ደርቢ ይጠበቃል፡፡
ባለፈው ሳምንት በሳንቲጎ በርናቦ 2ለ1 የተሸነፈው አትሌቲኮ ዛሬ ምሽት የመልሱን ጨዋታ በሪያድ ኤር ሜትሮፖሊታኖ ስታድዬም ያከናውናል፡፡
በላሊጋው ሪያል ማድሪድ ራዮ ቫልካኖን 2ለ1 አሸንፎ በተቃራኒው አትሌቲኮ በሄታፌ 2ለ1 ተሸንፎ የሚገናኙበት ጨዋታ ነው፡፡
ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በተደጋጋሚ መገናኘታቸው አይዘነጋም፡፡

ባለፈው ሳምንት ወደ ቤልጄየም ተጉዞ ክለብ ብሩዥን 3ለ1 አሸንፎ የተመለሰው የኡናይ ኢምሬው አስቶን ቪላ፣ ቪላ ፓርክ ላይ የመልሱን ጨዋታ የሚያደርገው ዛሬ ምሽት ነው፡፡
ሩብ ፍጻሜ መግቢያ በሩ ላይ የቆመው የሰሜን ለንደኑ አርሰናል በበኩሉ ኤምሬትስ ላይ የኔዘርላንድሱን ፒ ኤስ ቪ ይጋብዛል፡፡
ባለፈው ሳምንት በፊሊፕስ አሬና የተደረገውን ጨዋታ አርሰናል 7ለ1 በማሸነፉ ዛሬ በወጣት ተጨዋቾች ጨዋታውን እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
ፓሪሰን ዠርመን ከአስቶን ቪላና ክለብ ብሩዥ አሸናፊ፣ ባርሴሎና ከሊል እና ቦርሲያ ዶርትሙንድ አሸናፊ፣ የማድሪድ ደርቢ አሸናፊ ከአርሰናል እና ፒ ኤስ ቪ አሸናፊ እንዲሁም ባየርን ሙኒክ ከኢንተር ሚላን ጋር በሩብ ፍጻሜ የሚደረጉ ጨዋታዎች ይሆናሉ፡፡
በታምራት አበራ