የአየር ሁኔታን ለመመልከት የሚያግዙ ሦስት የራዳር ጣቢያዎች ዘንድሮ ወደ ሥራ ይገባሉ-የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

AMN – ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም

በ250 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ያለን የአየር ሁኔታ መመልከት የሚያስችሉ ሦስት የራዳር ጣቢያዎችን በተያዘው ዓመት ወደ ሥራ ለማስገባት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት፣ ተዓማኒነት ያለው የአየር ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት ዘመናዊ መሳሪያዎችን መጠቀም ላይ ትኩረት ተደርጓል።

የምልከታ ሥርዓቱን ለማጠናከርም በ250 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ያለ የአየር ሁኔታን የሚከታተሉ ራዳር ጣቢያዎች ተከላ ሥራ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መጀመሩን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ሙሉ ክፍል በዚህ የአየር ሁኔታ መመልከቻ መሳሪያ ለመከታተል ስምንት ራዳሮች እንደሚያስፈልጉም ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ሥራ የጀመረውን አንድ የራዳር ጣቢያን ጨምሮ በዚህ ዓመት የራዳር ጣቢያዎችን ብዛት አራት ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ፈጠነ ገልጸዋል።

እንደእሳቸው ገለጻ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የዓባይ ተፋሰስ አካባቢዎችን ለመመልከት የሚያስችል የራዳር ጣቢያ “ሻውራ” በተባለ አካባቢ ተተክሎ ወደ ሥራ ገብቷል።

በተመሳሳይ መካከለኛ ኢትዮጵያን ተደራሽ ለማድረግ በደብረ ብርሃን “እነዋሪ” በሚባል ቦታ ላይ የራዳር ተከላ ሂደት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ነው አቶ ፈጠነ የገለጹት።

በሌላ በኩል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልን ጨምሮ ምዕራብ ኦሮሚያና ቤንሻጉል ጉሙዝ እንዲሁም ጋምቤላ አካባቢ ያለውን የአየር ሁኔታ ለመመልከት የሚያስችል የራዳር ጣቢያ ተከላ ሥራ በቡኖ በደሌ ዞን “መኩ” ተራራ ላይ መጀመሩን አመልክተዋል።

በተያዘው ዓመት የታቀደውን አራት የምልከታ ራዳሮች ተከላን ለማሳካት በሀዲያ ዞን “ደንቦያ” በተባለ ቦታ ለመትከል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ጣቢያዎቹ ዓለም በደረሰበት ቴክኖሎጂ በመታገዝ የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እንደሚያስችሉ ገልጸው፣በቀጣይ አሥር ዓመታት ቀሪ ጣቢያዎችን በመትከል እንደ ሀገር ተደራሽነቱን ሙሉ ለሙሉ ለማድረግ ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢንስቲትዩቱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ባሉ አምስት ቆላማ ወረዳዎች በ15 ደቂቃ ልዩነት መረጃ የሚሰጥ ዘመናዊ የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያ ለመክፈት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ለዚህም ይረዳው ዘንድ ሰሞኑን ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚዛን አማን ከተማ መምከሩ ይታወሳል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review