AMN- መስከረም 10/2017 ዓ.ም
በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በአዲስ አበባ የተገነባው የብርሃን የአይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ባለፈው ዓመት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ይታወቃል።
ትምህርት ቤቱ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል ለማስተማር የተከፈተ ሲሆን፤ ምቹ የሆኑ የመማሪያ ክፍሎች፣ የመመገቢያ አዳራሾች ላይብረሪና ሌሎችም ዘመናዊ አገልግሎት መስጫ ክፍሎችን የያዘ ነው።
ብርሃን የአይነ ስውራን ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት በ2017 ዓ.ም ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ 312 ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ነው።
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሰላሌ ተወልዶ ያደገው ተማሪ ተስፋዬ ግርማ ትምህርቱን ተወልዶ ባደገበት አካባቢ እስከ አስራ አንደኛ ክፍል መማሩን ይናገራል።
ትምህርቱንም ሲከታተል የመማሪያ ክፍሎች አለመመቸት፣ የግብዓትና የመሰረተ ልማት ችግር እንዲሁም በሌሎችም ጉዳዮች ሳቢያ ትምህርቱን በአግባቡ መከታታል ተስኖት እንደቆየ ይናገራል።
መንግስት በሰጠው ዕድል በብርሃን የአይነ ስውራን ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብቶ መማር ከጀመረ ወዲህ እነዚያ ችግሮች ተቀርፈው የነገ ህልሙን እንዲያሰፋ እንደረዳው ተናግሯል።
በትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሃና አስማረ በበኩሏ ለትምህርቷ ካላት ጉጉትም ከሌላ አካባቢ አዲስ አበባ መጥታ ቤት በመከራየት ትምህርቷን ስትከታተል እንደቆየች ገልፃለች።
እንደ ብርሃን የአይነ ስውራን ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ሁሉ ሌሎችም በሀገሪቱ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ ከማስቻል አንፃር ብዙ መሰራት አለባቸው ብላላች።
ከሀዋሳ ከተማ የመጣውና በአዳሪ ትምህርት ቤቱ የ11ኛ ክፍል ትምህርት እየተከታታለ ያለው ተማሪ ቴዎድሮስ ሙሉጌታ በበኩሉ ትምህርቱን እንደልቡ ለመከታተል የትምህርት ቤት መሰረተ ልማቶችና ግብአት በበቂ ሁኔታ አለመደራጀቱ ፈተና ሆኖበት እንደቆየ ይገልፃል።
ነገር ግን አሁን ላይ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መሰረተ ልማት እና የትምህርት ግብዓት ባለው ብርሃን አይነስውራን ትምህርት ቤት ገብቶ መማር በመቻሉ ደስተኛ መሆኑን ይናገራል።
የብርሀን አይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ኤፍሬም አይተንፍሱ በበኩላቸው የ2017 ዓ .ም የመማር ማስተማር ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት ለአይነስውራን ተማሪዎች የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች በማሟላት እርስ በእርስ ትውውቅ እንዲኖራቸው መደረጉን ገልጸዋል።
ከተሰሩ ስራዎች መካከል ተማሪዎቹ ወደ ግቢው ሲገቡ የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ ማድረግና የትምህርት ግብአቶችን አስቀድሞ ማዘጋጀት ተጠቃሽ መሆናቸውን በቀጣይም ተማሪዎች ተሻለ እውቀት እንዲገበዩ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።