የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ 19ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ በተማሪዎች መካከል የጥያቄና መልስ ውድድር አካሄደ

AMN ህዳር 17/2017 ዓ .ም

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ 19ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ በተማሪዎች መካከል ከተማ አቀፍ የአሸናፊዎች አሸናፊ የጥያቄና መልስ ውድድር አካሂዷል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር፤ ትምህርት ቤቶች የዕውቀት ምንጭ ብቻ አይደሉም ብለዋል፡፡

ትምህርት ቤቶች የማህበረሰብና የሀገር ችግር የሚፈቱ ጥናትና ምርምሮች የሚካሄዱባቸው፣ ዘልማዳዊ አሰራርና አኗኗርን የሚለውጡ የፈጠራ ሀሳቦች የሚጠነሰሱባቸው፣ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ልማት፣ ለውጥና ዕድገት ምንጭ ሆነው የሚያገለግሉ ተቋማት ናቸው ብለዋል፡፡

መምህራን ሰውን የሚቀርጹ ሰዎች ሲሆኑ፣ ተማሪዎች የስርዓተ-ትምህርትና የመምህራን አሻራ ይዘው የሚያድጉ፣ የነገ ሀገር ዕጣ ፈንታ ወሳኝ፣ የምሁራንና የልሂቃን ችግኞች ናቸውም ብለዋል፡፡

በትውልድ ቅብብሎሽ፣ ዛሬና የዛሬ ትውልዶች የምንተካው በእነዚህ የዛሬ ተማሪዎች ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

በመሆኑም ይህን በዓል ምክንያት በማድረግ የተካሄዱ ውይይቶችም ሆነ የጥያቄና-መልስ ውድድሮች፣ በዕለት ተዕለት አኗኗራችን በአካባቢያችን እና ከምንመለከታቸው ጉዳዮች፣ በቀጣይ ከተማችንና የሀገራችን ዕጣ ፈንታ ላይ ባላቸው ተጽዕኖ እና ተጽዕኖዎችን በአወንታ ቅርጽ ለማስያዝ የትምህርት ማህበረሰቡ ባለው ሚና ላይ ጭምር ያተኮረ እንደነበረ አመላክተዋል፡፡

በሌላ በኩል የሀገር ፍቅር ያለውና ብዛሃነትን አውቆ የሚያከብር ትውልድ ለማፍራት ተማሪዎች ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ያሉት ደግሞ ምክትል አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሪት ፋኢዛ መሀመድ ናቸው።

ውድድሩ በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች የተደረገ ሲሆን በስነ ምግባር ፣ ግብረ ገብ ፣ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠሩ ጥያቄዎች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡

በውድድሩ ማጠቃለያም አሸናፊ ለሆኑ ተማሪዎች እውቅና እና ሽልማት መሰጠቱን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review