AMN – ሰኔ 03/2016 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በቦሌ ክፍለ ከተማ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ሥራ ላይ እየተሳተፉ ለሚገኙ ሠራተኞች ማዕድ በማጋራት ያበረታታ ሲሆን የምክር ቤቱ አባላት የኮሪደር ልማቱን ሒደት ጎብኝተዋል።
የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ብዜና አልከድር በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ከመቆጣጠር እና ከመከታተል ባለፈ በተለይ 24 ሰዓት እየተከናወነ ባለው የኮሪደሪ ልማቱ እየተሳተፉ የሚገኙ ሠራተኞችን ማበርታት ስለሚገባ የእራት ግብዣ ተደርጓል ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ በተባለው መንገድ እየሄደ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ምክር ቤት ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ማሾ ኦላና በበኩላቸው፣ የኮሪደር ልማቱ የሕዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ የሕዝብ ሀብት በአግባቡ ልማት ላይ መዋሉን ያሳየ ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ ደግሞ፣ የኮሪደር ልማቱ ከዚህ ቀደም ባለመናበብ ይከናወኑ የነበሩ የመሠረተ ልማት ግንባታን ችግር በመፍታት ተቋማት በአንድ ተናብበው የመሠረተ ልማት ዝርጋታን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ያከናወኑበት መሆኑን ተናግረዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ሺፈራው የኮሪደር ልማቱ በክፍለ ከተማው በሦስት አቅጣጫ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ሥራውን ሌት ተቀን እየሠሩ የሚገኙ ባለሙያዎችን እና ሠራተኞችን ማበረታታቱ ይበልጥ እንዲተጉ ያስችላል ብለዋል።
ምክር ቤቱ የማዕድ ማጋራቱን ያካሄደው በቦሌ ክፍለ ከተማ ሠዓሊተ ምሕረት፣ ከመገናኛ ኢምፔሪያል እና ከቦሌ ወሎ ሰፈር አካባቢ እየሠሩ ለሚገኙ ባለሙያዎች እና ሠራተኞች ነው። የምክር ቤቱ አባላት የኮሪደር ልማቱንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በሔለን ጀንበሬ