የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ባለፉት 6 ወራት በጤና ማጎልበት እና በሽታ መከላከል ዘርፍ የተሻለ አፈጻጸም አስመዝግቧል

AMN – ጥር 2/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ባለፉት 6 ወራት በጤና ማጎልበት እና በሽታ መከላከል ዘርፍ ‘የእናቶች እና ህጻናትን ጤና ከበጠበቅ፣ማህበረሰብ አቀፋ ጤና መድህን አገልግሎት እና በፈውስ ህክምና አገልግሎት ዘርፍ የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑ ተመልክቷል፡፡

ቢሮው በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዉ ግማሽ ዓመት የተከናወኑ ተግባራትን ገምግሟል።

ቢሮው የእናቶችን ጤና ከመጠበቅ አንፃር 246 ሺህ 192 የሚሆኑትን የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሰራቱና የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም የቤት ለቤት የምክር እና ድጋፍ አገልግሎት 208 ሺህ 749 እናቶችን መድረስ መቻሉ ተገልጿል።

ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ከመከላከል እና ከመቆጣጠር አንጻር 3 ሺህ 620 የቲቢ ፣ 1 ሚሊዮን 234 ሺህ 434 የደም ግፊት ፣ 223 ሺህ 784 የስኳር ፣ 50ሺህ 242 የማህፀን ጫፍ ካንሰር ልየታ ተደርጎላቸው አስፈላጊው ህክምና እና ክትትል እንዲያገኙ ማድረግ እንደተቻለ ተጠቁሟል።

ለኤች አይ ቪ ይበልጥ ተጋላጭነት አንጻር ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲመረመሩ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ፣ ተመርምረው ራሳቸውን ካወቁት እና ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኙት ውስጥ 89 በመቶ የፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት እንዲወስዱ ማድረግ ተችሏል ተብሏል፡፡

እንዲሁም የፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት ከሚወስዱ 96 በመቶ የሚሆኑት በአግባቡ በመውሰድ በደማቸው ውስጥ ያለውን የቫይረስ መጠን እንዲቀንሱ ማድረግ መቻሉ ተመላክቷል ።

በፈውስ ህክምና አገልግሎት በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት 118 ሺህ 910 የአስተኝቶ ህክምና ፣ 7 ሚሊዮን 800 ሺህ በላይ በተመላላሽ ህክምና አገልግሎት መስጠት የተቻለ ሲሆን ፣ የአንቡላንስ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ከነበሩት 3 ወደ 8 ማሳደግ መቻሉ እንዲሁሞ የህመም ማስታገሻ እንክብካቤ አገልግሎት አግኝተዋል ተብሏል፡፡

የድንገተኛ በሽታዎች ቅኝት እና መከላከልን በተመለከተ የኩፍኝ እና ሌሎች ወረርሽኝን ለመከላከል የተለያዩ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን እነዚህን ወረርሽኞች ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር እና የመከላከል ስራ መሰራቱ እንዲሁም 92 የጤና ጣቢያ ላብራቶሪ አገልግሎትን ባለ ሶስት ኮከብ እኖዲሆኑ ሆስፒታሎች ደግሞ ባለ አራት ኮከብ እንዲሆኑ መሰራቱ ተመላክቷል።

የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ቢሮው በግማሽ ዓመቱ ከፋይ አባላት እና ከተማ አስተዳደሩ መክፈል ለማይችሉ የማህበረሰብ ክፋሎች በድጎማ የተሸፈነላቸው በአጠቃላይ 1 ሚሊየን 330 ሺህ 562 አባወራ እና እማወራ መሆናቸዉ ተመላክቷል፡፡

የፋርማሲ አገልግሎትን በተመለከተ የህይወት አድን መድሀኒት 97 በመቶ የመሰረታዊ መድሀኒት አቅርቦት 96 በመቶ እንዲሁም የታዘዘውን መድሀኒት ሙሉ በሙሉ ያገኙ 94 በመቶ መሆናቸዉ ተመላክቷል።

የጤና አገልግሎትን ዲጂታል (ወረቀት አልባ) ለማድረግ በተሰራው ተግባር በሁሉም ሆስፒታሎችና በ51 ጤና ጣቢያዎች ላይ ተግባራዊ ማድረግ የተቻለ መሆኑ ተገልጿል።

ቢሮው ከመደበኛ ተግባራት ጎን ለጎን ባለፉት 6 ወራት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአቅመ ደካሞችን ቤት ዕድሳት’ የበጎ ፈቃድ የነፃ ህክምና አገልግሎቶች እና ሌሎች ተግባራት በትኩረት መከናወናቸዉ ተገልጿል ።

በግምገማው ላይ የቢሮው ምክትል ሃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዉ ግማሽ አመት አፈፃፀም ዉጤታማ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ህብረተሰቡ የሚፈልገዉን የጤና አገልግሎት መነሻ በማድረግ መተግበር እንደተቻለና የጤና አገልግሎት በጤናዉ ሴክተር ብቻ የማይሰራ በመሆኑ ቅንጅታዊ አሰራርን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ዶክተር ሙሉጌታ መናገራቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review