የአዲስ አበባ ከተማ የ2017 በጀት ከ230 ቢሊየን ብር በላይ ሆኖ ፀደቀ
AMN – ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የከተማ አስተዳደሩ የ2017 በጀት 230 ቢሊየን 398 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሆን በሙሉ ድምፅ አፀደቀ።
የሁለተኛ ቀን ጉባኤውን እያካሄደ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በዛሬው ውሎ ከተወያየባቸው አጀንዳዎች ውስጥ የከተማ አስተዳደሩ የ2017 በጀት አንዱ ነው።
ረቂቅ በጀቱን በዝርዝር ያቀረቡት የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን፣ የታክስ አፈፃጸም በጎ አዝማሚያዎችን ታሳቢ በማድረግ የከተማ አስተዳደሩ የ2017 በጀት 230.39 ቢሊየን ብር እንዲሆን መደረጉን አብራርተዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም የቀረበው ረቂቅ በጀት ላይ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎችም ምላሾች ተሰጥተዋል።
ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ከ2010 እና በ2011 እስከ 30 ቢሊየን ብር የነበረው ግብር አሰባሰብ ከዘንድሮው የገቢ አሰባሰብ አንፃር ስናየው እድገት ቢያሳይም ከተማዋ ልታመነጭ ከሚገባው አንፃር ብዙ መሥራት የሚጠበቅ በመሆኑ ግብርን በሐቀኝነት የመክፈል ባህልን ማዳበር ይገባል ብለዋል።
ከተማዋ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በርካታ የልማት ፍላጎቶች በመኖራቸው ከበጀት እጥረት አንፃር የመፈፀም እጥረት እንዳያጋጥም ብዙ መሥራት ይጠይቃል ነው ያሉት።
የታክስ መሠረት የማልማት ግብር ስወራን የመከላከል ቴክኖሎጂን የማዘመን እንዲሁም ታማኝ ግብር ከፋዮችን የማበረታታት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ወደግብር ሥርዓት ያልገቡ አንዳንድ የንግድ ማኅበራሰብ አባላት በሐቀኝነት ግብርን እንዲከፍሉ በማድረግ እና ደረሰኝ የማይቆርጡትን ወደ ሥርዓቱ በመመለስ ረገድ ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል።
አብዛኛዎቹ የከተማዋ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በታማኝነት እየከፈሉ በመሆኑም ከንቲባዋ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ምክር ቤቱ በበጀቱ ረቂቅ ላይ ያደረገውን ውይይት ተከትሎም የከተማ አስተዳደሩን የ2017 በጀት 230,398,009,300 ብር እንዲሆን በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።
በሽመልስ ታደሰ
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!