AMN – ታኅሣሥ 27/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከፍተኛ አመራሮች “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል ለሶስት ቀናት ሲያካሂዱት የነበረውን የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የቅድመ ጉባኤ ውይይታቸውን ማጠናቀቃቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ “ፓርቲያችን ብልጽግና ከምስረታው ጀምሮ ሀሳብን በማፍለቅ፣ ለህዝብ ቃል በመግባት እና በመተግበር አፈጻጸሙም ባህል ሆኖ እንዲዘልቅ በማድረግ ረገድ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል” ብለዋል።
በአንደኛው መደበኛ ጉባኤቸውንም ለህዝብ በገቡት ቃል መሠረት የፓርቲያውን ህብረ ብሔራዊ አንድነት ያጠናከሩበት፣ አካታችና አብሮነትን እንዲሁም አሳታፊ የፖለቲካ ስርዓትን በመዘርጋት ውጤት ያመጡበት መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ወቅታዊ እና ዉዝፍ ፈተናዎችን በመሻገር፣ የአመራር አንድነትን እና ቅንጅትን በማረጋገጥ ከተማችንን የስበት ማዕከል ያደረጉ ታላላቅ ፕሮጀክቶችንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጡ ሰው ተኮር ስራዎችን ማከናወን ችለናል ብለዋል።
ከዚህ በመነሳት በግንባር ቀደምትነት ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ተግባራትን ማከናወን የቻልን ሲሆን አመራሩ በተለወጠ የስራ ባህል የተግባር እና የአስተሳሰብ አንድነቱን አጠናክሮ እንደ ሀገርም እንደከተማም ለተመዘገቡ ውጤቶች ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል ሲሉም አክለዋል።
በቀጣይም በሁሉም መስኮች የተገኙ ውጤቶችን በማላቅ እንደ ድክመት የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የአሰራር ችግሮችን ደግሞ በዘላቂነት በመቅረፍ የሀሳብ ልእልናን በብቃት እየተገበርን በስራ አዳዲስ ባህል እየገነባን ለኢትዮዽያን ብልፆግና ተግተን እንሰራለን በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።