የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ስራ የጋራ ትጋት ውጤት በመሆኑ በሌሎችም የሀገሪቱ ከተሞች ለመተግበር ይሰራል- አቶ ጃንጥራር አባይ

You are currently viewing የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ስራ የጋራ ትጋት ውጤት በመሆኑ በሌሎችም የሀገሪቱ ከተሞች ለመተግበር ይሰራል- አቶ ጃንጥራር አባይ

AMN-መስከረም 20/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ በስኬታማነት እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ የጋራ ትጋት ውጤት በመሆኑ በዚሁ መንፈስ በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ለመተግበር እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።

አቶ ጃንጥራር በደሴ ከተማ በሚከናወነው የኮሪደር ልማት የቅድመ ዝግጅት ስራ ላይ ከከተማዋ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ።

የኮሪደር ልማት ስራ መንግስት ብቻውን ኃላፊነት የሚወስድበት አለመሆኑን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባው የደሴን የኮሪደር ልማት ስራ ስኬታማ ለማድረግ የ24/7 የስራ ባህል ከሁሉም ይጠበቃል ነው ያሉት።

ታሪካዊቷን ከተማ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ዘመናዊ እንድትሆን ከማድረግ አንፃርም ነዋሪዎች፣ ባለሀብቶችና ሁሉም አካላት ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል።

አዲስ አበባ ያለፈችበትን ተሞክሮ በማጋራት ከተማዋ ታሪካዊነቷን በጠበቀች መልኩ እንድትዋብም ይሰራል ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፣ የኮሪደር ልማቱ የህዝቡን የኑሮ ዘይቤ የሚቀይር እና ለነዋሪዎቿ የተመቸች፣ አገልግሎቷም የሰመረ ከተማን ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።

ከአዲስ አበባ ከተማ ሰፊ ተሞክሮ መገኘቱን በመጥቀስ ይህም ለፕሮጀክቱ ስኬት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰዋል።ሁሉም ለስኬቱ የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

በአፈወርቅ አለሙ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review