የኮሪደር ልማትን አጀንዳ አድርጎ መስራት ያስፈለገባቸው በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) ገለፀዋል።
የኮሪደር ልማት በቀዳሚነት የዜጎችን ጤና ከመጠበቅ አንፃር አስፈላጊ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በበርካታ ጥናቶች መሰረት እስከ 2050 ድረስ የከተማ ነዋሪ ከ50 እስከ 60 በመቶ ያድጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ከተማ ሊቀየር እና በፕላን ሊሰራ እንደሚገባው አስረድተዋል።
አደጋን ከመከላከል አንፃርም በነዋሪዎች የሚኖረውን የመንገድ ሽሚያ ለመቀነስ ከተማ ለሁሉም በሚል እሳቤ ከተማን መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኮሪደር ልማቱ ወደ ሌሎቹም የኢትዮጵያ ከተሞች መስፋፋት አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም በልኩ በፀዳ አካባቢ መኖር እንደሚገባው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እየተሰሩ ካሉ ስራዎች ውስጥ የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ይልቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደማሳያ የእንጦጦን የእርከን ስራ ጠቅሰዋል።
የኮሪደር ልማቱ የተሽከርካሪ መንገድ መጨናነቅና የትራንስፖርት ችግርን እንደሚቀርፍና ከገፅታ ግንባታ አኳያ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም አመላክተዋል።
የመብራት፣ የስልክና የፍሳሽ መስመሮችን አካቶ እየተሰራ የሚገኘው የኮሪደር ልማቱ ስራው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የሚስተዋለውን የመብራት ችግር ይቀርፋል ሲሉ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በራስ አቅም ያለምንም ብድር መሰራቱን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልማቱ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድልን እንደፈጠረም አመላክተዋል።
በሊያት ካሳሁን