የአዲስ አበባ የ2016 ዓ.ም እመርታዎች ሲታወሱ

You are currently viewing የአዲስ አበባ የ2016 ዓ.ም እመርታዎች ሲታወሱ

መዲናችን አዲስ አበባ በመጠናቀቅ ላይ ባለው የ2016 ዓ.ም በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲው እንዲሁም በተለያዩ መስኮች የተለያዩ ስኬቶችን አስመዝግባለች።

እኛም የዓመቱ መገባደጃ ላይ ሆነን ከተማዋ ካስመዘገበቻቸው ስኬቶች መካከል ዋና ዋናዎቹን ለማስታወስ ወድድን።

  1. ለምረቃ የበቁ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶች

በ2016 በጀት ዓመት ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት የበቁ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ ‘ለነገዋ’ የሴቶች የተሃድሶ እና የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል እንዲሁም የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ አንጸባራቂ ገድል የፈጸሙ ጀግኖችን የሚዘክር እና ተጋድሎውን የሚተርክ መታሰቢያ በመገንባት፣ የታሪክ ስብራትን በመጠገን ድሉን በሚመጥን መልክ ከፍ እንዲል ያደረገ ነው።

በመታሰቢያው ከየክልሎች ከተገኙት የተለያዩ ቅርሶች በተጨማሪ ከጣሊያን የመጣችው ፀሐይ አውሮፕላን ለጎብኝዎች ምቹ በሆነ ስፍራ ተቀምጣለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፕሮጀክቶች ሁሉ ትልቅ ሥራ የተሠራበት ስለመሆኑ የተናገሩለት እና ስብራቶችን የመጠገን አንዱ ፕሮጀክት፤ ‘ለነገዋ’ የሴቶች የተሃድሶ እና የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው በዚሁ እያገባደድነው ባለው 2016 ዓ.ም ነበር።

ማዕከሉ በዋነኛነት በሴተኛ-አዳሪነት ላይ የተሰማሩ ሴቶችን በመቀበል ሙያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ድጋፍ፣ ክትትል እና ሥልጠናዎችን በመስጠት ወደ ሥራ እንዲሰማሩ የሚያደርግ ሲሆን፣ በአንድ ዙር ብቻ 10 ሺህ ሴቶችን ተቀብሎ የማሰልጠን አቅም አለው።

ከዚህም ሌላ በ2016 በጉለሌ ክፍለ ከተማ እንጦጦ አካባቢ ለሚኖሩ ወገኖች ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው የጉለሌ የተቀናጀ ፕሮጀክት ይገኝበታል።

በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽ/ቤት የተገነባው ማየት ለተሳናቸው ወገኖች የአዳሪ ትምህርት ቤት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው በዚሁ በጀት ዓመት ነው።

በበጀት ዓመቱ ከ597 በላይ የሕፃናት መዋያ ቦታዎች በግል እና በመንግሥት ተቋማት የተገነቡ ሲሆን፣ ለልጆች 305 መጫወቻ ስፍራዎች ግንባታ ተከናውኗል።

በዚህ ዓመት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ከሆኑ ፕሮጀክቶች መካከል አዲስ የሥራ ባህልን ያስተዋወቀን እና በትጋት ከተሠራ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚቻል ከፍተኛ ልምድ የተገኘበት የኮርደር ልማት ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው።

በዚህም ከፒያሳ – አራት ኪሎ፣ ከሜክሲኮ ሳርቤት፣ የአራት ኪሎ – ቀበና – ኬኒያ ኤምባሲ፣ የመገናኛ – ሲኤምሲ አደባባይ፣ ከአራት ኪሎ ራስ መኮንን ድልድይ፤ ከደጎል አደባባይ – ቀይ ባህር ኮንደሚኒየም እና ከማህሙድ ሙዚቃ ቤት- በቴዎድሮስ አደባባይ እና ከቦሌ ድልድይ እስከ መስቀል አደባባይ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ዋንኞቹ ናቸው።

በበጀት ዓመቱ ከቤት ልማትና ማስተላለፍ ጋር በተያያዘ በ20/80 መርሐ-ግብር 2 ሺህ 87 ቤቶች፣ በ40/60 መርሐ-ግብር 2 ሺህ 966 ቤቶች፣ በወጪ ቆጣቢ እና በበጎ ፈቃድ 7 ሺህ 582 ቤቶች፣ ለኪራይ አገልግሎት 5 ሺህ ቤቶች በአጠቃላይ 17 ሺህ 635 ቤቶች በመንግሥት በጀት እና አስተባባሪነት ተገንብተው ለልማት ተነሺዎች እና ለሌሎች ተጠቃሚዎች ተላልፈዋል።

በ2016 ዓ.ም 43 የስፖርት ማዘውተሪያ እና 13 የመደመር ትውልድ የሕፃናትና የወጣቶች መጫወቻ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታቸው ተጠናቆ እና ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።

በተጨማሪም የቃሊቲ-ቱሉዲምቱ- ቂሊንጦ መንገድ ተሻጋሪ ድልድዮች፣ 3 ግዙፍ የገበያ ማዕከላት ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።

  1. ለከተማዋ እና ለከተማ አስተዳደሩ የተሰጡ እውቅናዎች

አዲስ አበባ በበጀት ዓመቱ በተማሪዎች ምገባ ለሌሎች ሀገራት ጭምር ልምድ ያጋራችበት እና እውቅና ያገኘችበት ዓመት ነበር።

በዚህም በፈረንሳይ ፓሪስ የተከናወነው እና በርካታ ሀገራት አባል በሆኑበት የዓለም የትምህርት ቤት ምገባ ጥምረት (School Meal Global Coalition) መድረክ ላይ ከተማችን አዲስ አበባ በሌሎች ሀገራት ልምድ የሚቀሰምባት ሆና ተመርጣለች።

በዓመቱ ከነበሩ ዓበይት ክንውኖች ሌላኛው በአሜሪካ ጆርጂያ ግዛት የሚገኘው ትሪኒቲ ኢንተርናሽናል አምባሳደርስ ዩኒቨርሲቲ ለከንቲባ አዳነች አቤቤ የሰጠው የክብር ዶክተሬት ዲግሪ እና የጆርጂያ ግዛት የሰጣቸው የክብር ዜግነት ሸልማት ትልቁ እና ዋንኛው ነበር ማለት ይቻላል።

መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገው እና በየዓመቱ በአፍሪካ ምርጥ ብቃት ያሳዩ አፍሪካዊያን መሪዎችን የሚሸልመው የአፍሪካ ሊደርሺፕ መጽሔት ከንቲባ አዳነች አቤቤን የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ሴት መሪ (African leadership magazine person of the year) ሽልማት አሸናፊ አድርጓቸዋል።

በሌላ በኩል በዓመቱ አዲስ አበባ ላይ እየተሠራ ባለው የስፖርት መሠረተ ልማት የማስፋፋት ተግባር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለከንቲባ አዳነች አቤቤ እውቅና ሰጥቷል።

እንዲሁም የዋልያዎቹ እና የሉሲዎቹ የበላይ ጠባቂ አድርጎም ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል።

በበጀት ዓመቱ ሴት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የኮሪደር ልማት እንዲሁም የነዋሪውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በከተማዋ የተሰሩ ሌሎች የልማት ሥራዎችን በማየት ለከንቲባ አዳነች አቤቤ እውቅና እና ሽልማት አበርክተዋል።

በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ለአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ስኬታማነት አስተዋፅኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት እውቅና መስጠታቸው ይታወሳል። 

  1. የዲፕሎማሲ ስኬቶች – የዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ተሳትፎ እና የዓለም እህትማማች ከተሞች ግንኙነትን ማጠናከር

በበጀት ዓመቱ ከተማ አስተዳዳሩ በትውልድ ግንባታ ዙሪያ እየሠራው ካለው ሥራ ልምድ ለመቅሰም የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የመጡ እንግዶችን አዲስ አበባ ተቀብላ አስተናግዳለች።

በዚህም “አዲስ አበባ፣ ሕፃናትን ለማሳደግ ምርጧ አፍሪካዊት ከተማ” በሚል መርሕ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ልምድ ለመቅሰም ወደ መዲናዋ የመጡ መሪዎች ትምህርት ቤቶችን እና ጤና ጣቢያዎችን ለህጻናት ምቹ ለማድረግ እና ለማሸጋገር በከተማ አስተዳሩ የተሠሩ ሥራዎችን ጎብንተዋል።

በበጀት ዓመቱ በከንቲባ አዳነች አቤቤ በሞሮኮ ማራኬሽ ከተማ በተካሄደው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች መድረክ ላይ ተሳትፈዋል።

ከዚህ ሌላ በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራ የልዑካ ቡድን በቻይና ጉብኝት ያደረገ ሲሆን ቡድኑ በጉብኝቱ በቻይና አስደናቂ እና ፈጣን ዕድገት ካስመዘገቡ ከተሞች ልምድ ወስዷል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እንዲሁም ከሚኒስትሮች ጋር በጋራ በመሆን በሩዋንዳ ባደረጉት ጉብኝት የአገሪቱን የከተማ ግብርናን እና የግብርና ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል።

ከንቲባ አዳነች በቆይታቸውም ከኪጋሊ ከተማ ከንቲባ ዱሴምግዩንቫ ሳሙኤል ጋር የእህትማማች ስምምነት ተፈራርመዋል።

በሌላ በኩል ከንቲባዋ በሲንጋፖር ከተማ በተካሄደው እና በርካታ የዓለም ከተሞች ተወካዮች ተገኙበት የዓለም ከተሞች  ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።

ጉባኤው ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹና አረንጓዴ በማድረግ፣ የአየር ብክለትን መከላከል እና የፈጣን ለውጥ ማዕከል በማድረግ ለትውልድ የሚተላለፍ ዐሻራ ስለማኖር በሰፊው የመከረ ሲሆን፣  ልምድ ልውውጥ እና መማማርን ማዕከል ያደረገ ጉባኤም እንደሆነ ይታወሳል።

በተጨማሪም ከንቲባ አዳነች አቤቤ በ ‘C 40’ አባል ከተሞች አማካይነት በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ በመሳተፍ በከተማዋ ቀጣይነት ያለው ዕድገት በማረጋገጥ ለኑሮ ምቹ ለማድረግ እየተሰሩ ባሉ ሥራዎች፣ ዕድሎች እና ተግዳሮቶች ዙሪያ ልምድ አካፍለዋል።

ከዚህም ሌላ በበጀት ዓመቱ በአዲስ አበባ ከተማ አመራሮች የልዑካን ቡድን በተለያዩ የዓለም ከተሞች ጉብኝት አድርገዋል።

በተለይ ቡድኑ በሲንጋፖር ባደረገው ጉብኝት በአረንጓዴ ልማት እና የከተማ ውበት ሥራዎች፣ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ዙሪያ የልምድ ልውውጥ አድርጓል።

በበጀት ዓመቱ የደቡብ ኮሪያ ቹንቾን ከተማ እና አዲስ አበባ 20ኛ ዓመት የእህትማማችነት በዓላቸውን በአዲስ አበባ ያከበሩ ሲሆን፣ የቹንቾን ከተማ ከንቲባ ዮክ ቶንግ ሃን እና የወጣቶች ዲፕሎማሲ ልዑካን ቡድናቸው በአዲስ አበባ ጉብኝት አድርገዋል።

የቻይናዋ የቾንቺን ከተማ አስተዳደር ኮንግረስ ሊቀመንበር ዣዎ ሺቺንግ እና የልዑካን ቡድናቸው በአዲስ አበባ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ ከከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

ከዚህም ሌላ የጣሊያን ቤርጋሞ ከተማ ከንቲባ ጆርጂዮ ጎሪ ከቡድናቸው ጋር በአዲስ አበባ በመገኘት የባህል ልውውጥ አድርገዋል።

ከንቲባ አዳነች ከዚህም ሌላ  የአዲስ አበባ እህት ከተማ ከሆነችው የቻይናዋ ቤጂንግ ከተማ ኮሚኒስት ፓርቲ ምክትል ዋና ጸሐፊ እና የቤጂንግ የአመራር ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንት ከሆኑት ሚስተር ሊ ዌይ ከተመራው የልዑካን ቡድን አባላት ጋር ተወያይተዋል።

አዲስ አበባ እና የቻይናዋ ርጃው ከተማ የእህትማማችነት ግንኙነት ለመመስረት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት  ተፈራርመዋል።

በዓመቱ በአዲስ አበባ እና በጀርመኗ ላይፕዚሽ ከተማ የ20ኛ ዓመት የእህትማማችነት፣ የአጋርነት ግንኙነትን በማስመልከት በላይፕዚሽ ከተማ በአዲስ አበባ ስም አደባባይ ተሰይሟል።

  1. በማኅበራዊ አገልግሎት የተገኙ ስኬቶች

በበጀት ዓመቱ የአዲስ አበባን የብዙኃን ትራንስፖርት አቅርቦት ለማሻሻል ተጨማሪ 67 የከተማ አውቶቢሶች ወደ ሥራ ገብተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩበትም ነው።

በከተማዋ ለኑሮ አመቺ ያልነበሩ አካባቢዎችን በማፍረስ በአጭር ጊዜ መልሰው የተገነቡ እና የታደሱ 907 ቤቶች ለነዋሪዎች የተላፉበት እና አዳዲስ ግንባታዎችም የተጀመሩበት ዓመትም ነበር 2016።

በበጀት ዓመቱ 435 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለመምህራን በዕጣ እንዲተላለፉ ተደርጓል።

በሌላ በኩል “ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ሐሳብ እንደ ሀገር የተጀመረው ንቅናቄ በመዲናችን አዲስ አበባ በስፋት የተከናወነበት እና ለውጥም የታየበት ነው።

በሕግና በአሠራር የአየር ብክለትን ለመቀነስ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተሠርተዋል።

ከንቅናቄው ጎን ለጎን ከ150 በላይ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ በሀገራችን የተገጣጠሙ ሚኒባሶች ከማዕከል እስከ ወረዳ ለሚገኙ ተቋማት ተከፋፍለዋል።

በመገባደድ ላይ ባለው በጀት ዓመት ለዘመናት ልዩነቶችን በኃይል እና በጠብ መንጃ ከመፍታት ታሪክ በመውጣት እና በሠለጠነ መንገድ በውይይት ለመፍታት ያግዛል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር  የተጀመረው በአዲስ አበባ ነበር።

በዚህም በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን፣ የአጀንዳ ልየታም ተካሂዷል።

በበጀት ዓመቱ የከተማ ሕዝብ ድምፅ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የአዲስ ቻናል፣ የብራንዲንግ ሥራ እና የታለንት ሾው በደማቅ ሥነ-ሥርአት ይፋ ያደረገበት ዓመት ነው።

በዚህም ሚዲያው የከተማዋ ነዋሪዎች ዐይንና ጆሮ በመሆን ለውጥ በማምጣት፣ መረጃን በመስጠት፣ በማስተማር እና በማዝናናት ሂደት ውስጥ የራሱን አዎንታዊ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ እና የብዝኃነትና የትውልድ ድምፅ መሆኑን በተግባር ያሳየበት መሆኑ የተመሰከረበት ነው።

የ5ኛ ዙር አረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር እንደ አዲስ አበባ ከተማ የተካሄደ ሲሆን፣ በከተማ ሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ አምባሳደሮች አና ዲፕሎማቶች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አትሌቶች፣ የተለያዩ ስፖርት ቤተሰቦች እንዲሁም ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው ዐሻራቸውን አኑረዋል።

በዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ ደረጃ 9.9 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በመትከል ከዕቅድ በላይ ስኬት የተመዘገበበት ነው።

በሰለሞን በቀለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review