AMN-መስከረም 22/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ 5 ሺህ 300 የቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን በተለያዩ መስፈርቶች ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄሎ ኡመር (ዶ/ር)፤ የዘንድሮውን ዓመት የተማሪዎች ቅበላና አጠቃላይ ዝግጅቱን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ መሆኑን ተከትሎ ተማሪዎችን በራሱ መስፈርት ተቀብሎ ለማስተማር በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው የውድድር መስፈርት የተማሪዎችን ብቃት፣ የመግቢያ ፈተናን ማለፍና ሌሎችንም መስፈርቶች ማእከል ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ 5 ሺህ 300 የቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን በመስፈርቶቹ አወዳድሮ ለማስተማር ተዘጋጅቷል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ አስመዝግበው በመንግስት ሙሉ ወጪ የሚማሩ 4 ሺህ 402 ተማሪዎች ለውድድር ተመዝግበው 2 ሺህ 660 የመግቢያ ፈተናውን ማለፋቸውን ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲ የመግቢያ ነጥብ በማምጣትና በራሳቸው ከፍለው ለመማር ካመለከቱት 7 ሺህ 537 ተማሪዎች መካከል ደግሞ 2 ሺሀ 640 ተማሪዎች የመግቢያ ፈተናውን አልፈዋል ብለዋል።
በመሆኑም በተያዘው ዓመት ዩኒቨርሲቲው በድምሩ 5 ሺህ 300 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል ከ500 በላይ ውጤት ላስመዘገቡ 200 ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል የሚያገኙ መሆኑንም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በአዲሱ የተማሪዎች ቅበላ መስፈርት መሰረት ሴቶችንና አካል ጉዳተኞችን በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ አሰራሮች ተግባራዊ መደረጋቸው ታውቋል።