AMN – ጥር- 18/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ለወሊድ እና ድንገተኛ ህክምና አገልግሎት የሚውሉ 13 የአምቡላንስ ተሽከርካሪዎችን በስሩ ለሚገኙ ጤና ተቋማት አስተላለፈ፡፡
ቢሮው አምቡላንስ ተሽከርካሪዎቹን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘ ሲሆን በከተማዋ የሚሰጠውን የወሊድ እና ድንገተኛ ህክምና አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ ለመስጠት ያግዛልም ተብሏል፡፡
አምቡላንስ ተሽከርካሪዎቹን ለየክፍለ ከተሞቹ ያስረከቡት የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሃንስ ጫላ፣ አዳዲሶቹን ጨምሮ በከተማዋ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ አምቡላንሶች ቁጥር ከ106 መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ይህም ከ5 ዓመታት በፊት በከተማዋ አገልግሎት ይሰጡ ከነበሩ አምቡላንስ ተሽከርካሪዎች ቁጥር በሶስት እጥፍ የሚበልጥ ነው ብለዋል፡፡
አምቡላንሶቹን የተረከቡ የጤና ተቋማት ተሽካሪዎቹን ለታለመላቸው አላማ በማዋል የሚሰጡትን የወሊድ እና ድንገተኛ ህክምና አገልግሎት እንዲያሻሽሉም የቢሮ ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡
ተሽከርካሪዎቹን የተረከቡ የየክፍለ ከተሞቹ የጤና ፅ/ቤት ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ ድጋፉ የሚሰጡትን የጤና አገልግሎት ለማቀላጠፍ የሚረዳ መሆኑን ገልፀው ለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአሰግድ ኪዳነማርያም