የአፋር ህዝብ በለውጡ ሰባት ዓመታት ፈተናዎችን በፅናት በማለፍ አበረታች የልማት ድሎችን ለመቀዳጀት መቻሉን ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።
በሠመራ ከተማ “ትናንት ዛሬና ነገ ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ ሐሳብ የለውጡን ሰባት ዓመታት ጉዞ የተመለከተ የማጠቃለያ ውይይት ዛሬ ተካሄዷል።
በዚህ መድረክ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ባለፉት ሰባት ዓመታት ፈተናዎችን በፅናት በማለፍ አበረታች የሚባሉ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ በተምሳሌትነት የሚጠቀሱ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
በክልሉ በለውጥ ዓመታት በርካታ የልማት ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው ይሄንን አጠናክሮ ማስቀጠሉ ላይ ትኩረት እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው በክልሉ ባለፉት ሰባት ዓመታት ገዢ ትርክትን በማስረፅ ረገድ ይበል የሚያሰኝ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
ፓርቲው አካታችና አሳታፊ ስርዓትን በመተግበር ዜጎች እኩል ተሳታፊ የሆኑበትን ስርዓት እውን ከማድረግ ባሻገር ውሳኔ ሰጪነት ሊጎለብት መቻሉን አብራርተዋል።
በክልሉ ያልተለመዱ የግብርና አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግም ከዚህ ቀደም ጾም ያድሩ የነበሩ የክልሉ አካባቢዎችን በማልማት የተለያዩ አዝዕርትና ፍራፍሬዎችን ለማምረት መቻሉ የለውጡ ፍሬ መሆኑንም ገልፀዋል።
በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች መገኘታቸዉን ከብልጽግና ፖርቲ ጽ/ቤት ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።