የአፋር ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ተጀመረ

You are currently viewing የአፋር ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ተጀመረ

AMN-መስከረም 21/2017 ዓ.ም

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ፣የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ፣የኮሚሽኑ አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት በሰመራ ከተማ የምክክርና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተጀምሯል።

ለምክክሩም ከ49 ወረዳዎች የተውጣጡ 802 የህብረተሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።

የሀገር ሽማግሌዎች፣የጎሳ መሪዎች፣ሴቶች፣ወጣቶችና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል የወከሉ ተሳታፊዎች እንደ ክልል የያዟቸውን አጀንዳዎች ለምክክር ያቀርባሉ።

የአጀንዳ ማሰባሰብና ለሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚሳተፍ ተወካዮችን የመለየት ሂደቱን ያስጀመሩት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አይሮሪት መሐመድ (ዶ/ር) በምክክር ተሳታፊ ልየታ ሂደቱ አካታችነትን መርህ በማድረግ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች በፍትሀዊነት ማሳተፍ ተችሏል ብለዋል።

በክልሉ የሀገር በቀል እውቀቶችን በመጠቀም ለምክክሩ ሂደት ስኬታማነት አግዘዋል ብለዋል።

ሀገር ለገጠማት ልዩነቶች ዘላቂ ሰላምን ለማምጣትና የጋራ ቤትን በጋራ ለመገንባት የሚያስችል የምክክር ምዕራፍ መሆኑን ያወሱት ኮሚሽነሯ ተሳታፊዎቹም የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ለስኬታማነቱ ሊተጉ ይገባል ብለዋል።

ከ9 የማህበረሰብ ክፍሎች የተወከሉ 802 ተሳታፊዎች በቡድን በመከፋፈል ለሶስት ቀናት ምክክር ካካሄዱ በኋላ በየማህበረሰቡ የሚወክሏቸውን 6 አባላት ለሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በመምረጥ ያጠናቅቃሉ።

ቀጥሎም ከ700 በላይ ተሳታፊዎችን የያዘው የባለድርሻ አካላት ውይይት እንደሚካሄድ የምክክር ኮሚሽኑ ያወጣው መርሀ ግብር ያመላክታል።

በፍቃዱ መለሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review