የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

You are currently viewing የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

AMN ህዳር 20/2017 ዓ.ም

የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ለምታከናውነው ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

የአፍሪካ ልማት ባንክ 60ኛው ዓመት የምስረታ በዓል በአዲስ አበባ ተከብሯል።

በክብረ በዓሉ የባንኩ ከፍተኛ አመራሮችና የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የባንኩ የምስራቅ አፍሪካ ክልል ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ሊያንድሬ ባሶል (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ባንኩ የአፍሪካን ልማት ለማረጋገጥና ከድህነት ለመውጣት የሚያግዙ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል።

አሁንም ባንኩ የአፍሪካን ልማት በመደገፍ የአህጉሪቱን ልማት የሚያረጋግጡ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ነው ያብራሩት።

በተለይም የመንገድ መሰረተ ልማቶች፣ የኃይል፣ ትራንስፖርት፣ ግብርና፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችን የሚያግዙ የተለያዩ ሥራዎችን በአህጉሪቱ እንዲከናወኑ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ባንኩ በአፍሪካ አህጉር የሚሰሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በመደገፍ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ ለሚሰሩ ፕሮጀክቶች ድጋፍ በማድረግ ትምህርት ቤቶች፤ መንገዶች፤ የጤና ተቋማትንና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እውን ለማድረግ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፤ እውን ማድረግም ችሏል ሲሉ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ለምታከናውነው ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላቸው ባንኩ በኢትዮጵያ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ የአገሪቱን ልማት እየደገፈ ይገኛል ብለዋል።

በአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በኢትዮጵያ መሠራታቸውንም ተናግረዋል።

ባንኩ በኢትዮጵያ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቁመው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review