AMN- መስከረም 30/2017 ዓ.ም
የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ ከጥቅምት 5 እስከ 7 በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
“አፍሪካ፤ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ፀጥታና ሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ ከጥቅምት 5 እስከ 7 በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ጉባዔውን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው ጉባዔው “አፍሪካ፤ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ፀጥታና ሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
በጉባዔው አህጉራዊ የፀጥታ ማዕቀፎችን ማጠናከርና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ሸብርተኝነትን ለመዋጋትና የጋራ ደህንነት ስጋቶችን ለመፍታት አጋርነትን ስለማጠናከር እና በመከላከያ ኢንዱስትሪ መስክ አብነት የሆኑ አገራት ተሞክሮዎች የሚጋሩበት ነው ብለዋል።
ጉባዔው አፍሪካ ለዓለም ሰላም መረጋገጥ በሰላም ማስከበር ያላትን ሚና ስለማሳደግ እና በሰብዓዊ ዕርዳታና በአደጋ ወቅት ያለውን የትብብር አቅም በማሳደግ ላይ ያተኩራል ነው ያሉት።
በአቅም ግንባታ መስክ የመከላከያ ተቋማትን በስልጠና፣ በቴክኖሎጂና በዕውቀት ሽግግር ማጎልበት በሚያስችሉና በሌሎች ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ይመክራል ብለዋል።
በጉባዔው የአፍሪካን የወደፊት የመከላከያ ስትራቴጂ ለመቅረጽ የሚያስችሉ ጥልቅ የጥናት ውጤቶችን የሚያቀርቡ ታዋቂ ሰዎች መጋበዛቸውን አመላክተዋል።
በጉባዔው ላይ ከሚካሄዱ ውይይቶች በተጓዳኝ የአፍሪካን የትናንት፣ የዛሬና የነገ ወታደራዊ ጉዞዎች፣ የአፍሪካን የሰላም ማስከበር አስተዋፅኦ እንዲሁም የሳይበር ደህንነትንና ወቅታዊ ትብብሮች እና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚያመላክቱ ዘጋቢ ፊልሞች፣ ኤግዚቢሽንና ጉብኝቶች እንደሚካሄዱ ጠቅሰዋል።
መድረኩ የአፍሪካን የወደፊት ሰላምና ብልፅግና እንዲሁም በጋራ ፀጥታ ላይ የወደፊት አቅጣጫን የሚያመላክቱና ቀጣናዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የጋራ ትብብር የሚፈጠርበት ነው ብለዋል።
በጉባዔው ላይ የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች፣ ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ የሆኑ ወታደራዊ አታሼዎች፣ በወታደራዊ ጥናትና ምርምር ከፍተኛ አቅም ያላቸው ምሁራን ፣ ወታደራዊ ጠበብቶችና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እንደሚገኙ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡