የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የፋይናንስ ምንጭና የልማት አቅም እየሆነ ነው -የኢኒሼቲቩ ሊቀ መንበር አህመድ ሽዴ

AMN- ህዳር 6/2017 ዓ.ም

የአፍሪካ ቀንድ ኢንሼቲቭ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የፋይናንስ ምንጭና የልማት አቅም መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትርና የኢንሼቲቩ ሊቀ መንበር አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተባባሪነት የተጀመረው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ከተመሰረተ አምስት አመት ሊሆነው ነው፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰባት የምሥራቅ አፍሪካ አገራት የተመሰረተው ኢንሼቲቭ በየአገራቱ የፋይናንስ ሚኒስትሮች ይመራል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የተመሰረተ ተቋም እንደሆነም ይታወቃል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትርና የኢኒሼቲቩ ሊቀ መንበር አህመድ ሽዴ፤ ኢኒሼቲቩ በቀጣናው የኢኮኖሚ ትብብር፣ሰብዓዊ ልማት እና ሌሎችም ዘርፎች ላይ በትብብር ለመስራትና የሚያጋጥሙ ችግሮችንም በጋራ ለመፍታት የተመሰረተ ፕሮጀክት መሆኑን አስረድተዋል።

የቀጣናውን አገራት በባቡር፣መንገድ፣ ኢነርጂ እና መሰል መሰረተ ልማቶች ለማስተሳሰር እንዲሁም የድርቅ፣ ጎርፍና የሌሎችም አደጋዎችን ተጋላጭነትን በጋራ ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

የቀጣናውን አገራት የንግድ ልውውጥ ለማሳለጥ የጋራ የጉምሩክ ጣቢያዎች ተመስርተዋል ሲሉም ተናግረዋል።

በአምስት ዓመታት ከ15 ቢሊየን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ፕሮጀክቶች ተቀርጸው እስካሁን 10 ቢሊየን ዶላር ሥራ ላይ መዋሉንም አረጋግጠዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የኢኒሼቲቩ ተጠቃሚ መሆኗን ጠቅሰው፤ የመኢሶ – ድሬዳዋ ፍጥነት መንገድ እንዲሁም የአዲስ – ጅቡቲ ኮሪደርን በምሳሌነት አንስተዋል።

በጅቡቲ፣በኬንያና ሌሎችም የቀጣናው አገራት የሚሰሩ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቁመው፥ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳንን የሚያገናኘው የመንገድ ፕሮጀክትም በዚሁ ኢኒሼቲቭ እንዲካተት ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ለቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲሁም ለአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ቀጣይነት ኢትዮጵያ የተጠናከረ ድጋፍ ታደርጋለች ሲሉም አረጋግጠዋል።

ኢኒሼቲቪ በዋነኝነት በዓለም ባንክ የሚደገፍ ቢሆንም የአፍሪካ ልማት ባንክ፣የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም አገራት በአጋርነት የሚሳተፉበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የፋይናንስ ምንጭና የልማት አቅም መሆኑን ጠቅሰው፥ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው ጋር በተሳሰረ መልኩ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የአምስት አመት አፈፃፀሙን ለመገምገምና የቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ በመጪው ታህሳስ ወር በአዲስ አበባ ስብሰባውን የሚያደርግ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review