የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የቱሪዝም ፍሰት እና የባህል ልውውጥ እንዲኖር ያስችላል- የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሽ ግርማ

AMN – ታኀሣሥ 4/2017 ዓ.ም

የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ለኢትዮጵያ ከሚያስገኘው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜታ ባሻገር የቱሪዝም ፍሰት እና የባህል ልውውጥ እንዲኖር እንደሚያስችል የኢፌዴሪ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሽ ግርማ ገለጹ፡፡

38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት እንዲካሄድ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና ከተለያዩ ከ40 በላይ ከሆኑ ተቋማት ለተውጣጡ የቪ አይ ፒ ሹፌሮች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሽ ግርማ ስልጠናውን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፣ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ለሀገራችን ከሚያስገኘው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜታ ባሻገር የቱሪዝም ፍሰት እና የባህል ልውውጥ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

በ38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ሚኒስትሮች፣ ከሌሎች አህጉራት የሚጋበዙ የሀገራት መሪዎች እና በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የሚሳተፉበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም እንግዶች ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጀምሮ እስከ ማረፊያ ሆቴሎች ድረስ ጉባኤው እስኪጠናቀቅ የእጀባ እና የጥበቃ ሥራ እንዲሁም በቱሪዝም መዳረሻዎች ለክብራቸው የሚመጥን የመስተንግዶ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስልጠና እንደሆነ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ሙያ ቴክኒክ ኮሌጅ የአሽከርካሪ ስልጠና ዲፓርትመንት ኃላፊ ኮማንደር ወ/ሩፋኤል አምባዬ በበኩላቸው፣ በስልጠናው ከ40 በላይ የተቋማት የቪ አይ ፒ ሹፌሮች እንደሚሳተፉ በመግለጽ ጉባኤው ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ስኬታማ እንዲሆንና የሀገራችንን ገጽታ የሚገነባ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review