ምሥረታ
ለአፍሪካ ነፃነት በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩት ሕዝቦች ብቻ ሳይሆኑ በነፃነት ጥላ ሥር የነበሩት አፍሪካዊያን ጭምር በቅኝ ግዛት ሥር ሲማቅቁ ለነበሩ ወገኖች ነፃነት ብዙ መታገል ነበረባቸው።
የአህጉሪቱ መሪዎች በዓለም መድረክ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ነፃ ላልወጡ ወንድም አገሮች ሉዓላዊነት በሁለት ቡድን ተከፍለው ትግላቸውን ጀመሩ።
በአንድ በኩል ራሱን “የዘመናዊ ተራማጅ” ብሎ የሚጠራው፣ በጋናው ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማ የሚመራው የ“ካዛብላንካ ቡድን” ተመሠረተ። ይህ ቡድን የአህጉሪቱን መንግሥታት በኅብረት ማዋሃድን ዓላማ ያደረገ ሲሆን አባላቱም ጋና፣ አልጄሪያ፣ ጊኒ፣ ሞሮኮ፣ ግብጽ፣ ማሊ እና ሊቢያ ነበሩ።
ሁለተኛው ቡድን የ”ሞንሮቪያ ቡድን” ሲሆን የተመራው በሴኔጋል ፕሬዚዳንት ሊዮፖልድ ሴዳር ሴንግሆር ነበር። አባላቱ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ፣ ላይቤሪያ እና ኢትዮጵያ ሲሆኑ የእነሱ የኅብረት ዓላማው ረጋ ባለ ሁኔታ ኅብረቱን ወደ አንድነት ማምጣት የሚል ነበር።
መጨረሻም በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ከተማ ይፍሩ ታላቅ ጥረት እና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ ሁለቱም ወገኖች አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው በፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር ግንቦት 25/1963 ነበር በ32 ፈራሚ ሀገራት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሠረተው።

ድርጅቱ አዲስ አበባ ላይ ሲመሠረት ለስብሰባው ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉት በጊዜው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ልዑካን መሪ የነበሩት ተስፋዬ ገብረ እዝጊ (ዶ/ር) ነበሩ። በዚያው ስብሰባ ላይ ቋሚ ዋና ጸሐፊ እስኪገኝ ድረስ ተመርጠው ለአንድ ዓመት ያገለገሉት ኢትዮጵያዊው አቶ ክፍሌ ወዳጆ ነበሩ።
ዓላማ
የጸረ ቅኝ ግዛት ትግሎችን ለመደገፍ፣ አፍሪካዊያንን ማስተሳሰር እና ችግሮቻቸውን መፍታት የዚሁ ተቋም ዋና ዋና ዓላማዎች ነበሩ። እናም ድርጅቱ ከነፃነት ትግል ባሻገር የበለጸገች አፍሪካን እውን ማድረግ ብሎም የአፍሪካን የኢኮኖሚ፣ የባህል እና የፖለቲካ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ትልቁ ዓላማው ነበር።
የአፍሪካ ኅብረት (AU) ምሥረታ
የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች እ.ኤ.አ በ2002 በደርባን ባካሄዱት ጉባዔ ላይ በአህጉሪቱ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህል እና በማኅበሪዊ መስኮች ለውጥ ለማምጣት ግቦችን አስቀመጡ።
በዚህም የአፍሪካ ኅብረት በሚል የስያሜ ለውጥ አደረጉ። ኅብረቱ አሁን ላይ 55 አባላት አገራትም አሉት።

ስኬት ከተግዳሮት
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በቆይታው በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ የአፍሪካ ሀገራት ነፃ እንዲወጡ እገዛ ማድረጉ፣ አፍሪካዊያን የሚሰባሰቡበት እና የሚመክሩበት ተቋም መሆኑ፣ በተወሰኑ ሀገራት መካከል ግጭቶች ሲከሰቱ በውይይት ለመፍታት መሞከሩ እና የሰላም ችግር ባለባቸው ሀገራት ሌሎች ተቋማትን እና ሀገራትን በማስተባበር ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲገባ ማድረጉ ትልቁ ስኬቱ ተደርጎ ይወሰዳል።
ይሁን እንጂ የአህጉሪቱ አባቶች መሠረት አድርገው የተነሱለት ዓላማ አብዛኛው ግቡን ቢመታም አሁንም ድረስ አፍሪካ ያልተሻገረቻቸው እንቅፋቶች ከፊቷ እንደተደቀኑ ናቸው የሚሉት ይበረክታሉ።
አፍሪካ በሌሎች አህጉራት የማይገኙ ውድ የፋብሪካ ጥሬ ዕቃዎችን አሁንም በርካሽ እየላከች የፋብሪካ ውጤቶችን ደግሞ በውድ ዋጋ ታስገባለች።
የአውሮፓ ምርት ማራገፊያነቷ አሁንም እንደቀጠለ ነው የሚሉ በርከት ያሉ አስተያየቶች እንደተጠበቁ ሆነው የአፍሪካዊያን የእርስ በርስ ንግድ ዝቅተኛ እንደሆነ እና አፍሪካዊያን እርስ በርስ የንግድ ግንኙነት ከመመሥረት ይልቅ ወደ አውሮፓ መላክ እንደሚቀናቸው የሚገልጹ አስተያየቶች ሚዛን የሚደፉ ናቸው።
አፍሪካ በቀል የሆኑ የንግድ፣ አቪየሽን፣ ቴክኖሎጂ እና ሌሎች አስፈላጊ ተወዳዳሪ ተቋማት ጥቂት ናቸው የሚሉ የመብዛታቸውን ያህል እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን መላክ እና የንግድ እና የቢዝነስ ሥራዎችን ማቀላጠፍ የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች ላይ ካልተሠራ የአፍሪካ ዘመናዊ ቅኝ ግዛት መቀጠሉ አይቀሬ ስለመሆኑ የሚናገሩ መብዛታቸው የጉዳዩን አሳሳቢነት ያጎላዋል።
ኅብረቱ ዛሬም ቢሆን በብዙ መልኩ ከምዕራባዊያኑ ተፅዕኖ መላቀቅ አለመቻሉ የድክመቱ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

የኢትዮጵያ ሚና ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት እስከ አፍሪካ ኅብረት ምሥረታ
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በኢትዮጵያዊው ንጉሥ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ እና በጋናው የነፃነት ታጋይ ክዋሚ ንኩሩማህ አሸማጋይነት በአዲስ አበባ እንዲመሠረት ትልቁን የመሪነት ድርሻ እንደተጫወቱ ታሪክ ያስረዳል።

ነፃነቷን አስከብራ በኖረችው ኢትዮጵያ እና ሌሎች ከቅኝ ግዛት ነፃ በወጡ የአፍሪካ አገራት የተመሠረተው ድርጅቱ፣ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ እና ለሌሎቸም ነፃ መሆን ጥረት ያደረገችው ኢትዮጵያ የአባል ሀገራቱ መሰባሰቢያ ቤታቸው ናት።
የአፍሪካ ኅብረትን በመመሥረት ሂደት ኢትዮጵያ ሁለት ድሎች እንዳስመዘገበች ይወሳል። አንዱ ኅብረቱን መፍጠር ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የኅብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲሆን የነበረው ትግል እና ስኬቱ ነው።
ከዚያም በኋላ ሁሉም የአገሪቱ መሪዎች ለድርጅቱ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡ በማድረግ ኢትዮጵያ ለኅብረቱ ዕድገት እና ጥንካሬ ትልቁን አበርክቶ አድርጋለች።
በዚህም በኢትዮጵያ ታሪክ ሁሉም መንግሥታት ምንም ዓይነት የዓላማ መዛነፍ ሳያሳዩ ለአፍሪካ አንድነት መጠናከር ያላቸውን ፅኑ አቋም አሳይተዋል። ለዚህም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማረጋገጥ ጭምር ከአፍሪካ አህጉር አባል ሀገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ጉዳዩን በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ እና ስትራቴጂዋ በማካተት ተግባራዊ ስታደርግ ቆይታለች።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረት መጠናከር ካላት የረጅም ዘመን ተነሣሽነት፣ ሀገራዊ ታሪክ፣ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር፣ ከምትገኝበት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ፣ ወታደራዊ ጥንካሬ፣ እየጨመረ ከሚመጣው ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ፣ በአህጉሪቱም ሆነ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ፣ ሰላም እና ደኅንነት ላይ ከምታበረክተው አስተዋፅኦ አንጻር በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ ያላት ተጽዕኖ ፈጣሪነት እየጨመረ መምጣቱ እንደ ዋንኛ አብነት ይነሣል።
በአጠቃላይ የአፍሪካዊያን አንድነት መጠናከር ለኢትዮጵያ ቀዳሚ እና የማያወላውል አጀንዳዋ ነው።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረት መጠናከር ያላት ፍላጎት በሁኔታዎች ላይ የሚመረኮዘ አለመሆኑ እና የአፍሪካ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ ስለመሆኑ ብዙ አመለካች አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል።
እንደወትሮው ሁሉ ኢትዮጵያ ዘንድሮ ለሚካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ያደረገች ሲሆን ጉባኤው መጪው የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም፤ 46ኛው የኅብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ደግሞ ቀደም ብሎ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄዱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው። ከነዚህ ጥቅሞች መካከልም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ጉዳዮች ያላትን የማይናወጥ ፅኑ አቋም ግልጽ ለማድረግ፣ የኢትዮጵያን መልካም ሁኔታ ለአፍሪካውያን እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተግባር ለማሳየት እና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት መልካም አጋጣሚን ይዞ እንደሚመጣ ይታመናል።
በሰለሞን በቀለ