AMN- ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም
ተለዋዋጭና ውስብስብ እየሆነ የመጣውን የአፍሪካ ደህንነት ፈተና በዘላቂነት ለመፍታት አፍሪካዊያን የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀረበ
የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
“አፍሪካ በጠንካራ አንድነት ለሁለንተናዊ ፀጥታና ሰላም” በሚል መሪ ቃል በተጀመረው በዚህ ጉባዔ አህጉሩን እየፈተኑ ያሉ የሰላም ፀጥታ ችግሮች እንዲሁም የመፍቻ አማራጮች ዙሪያ ምክክር ይደረጋል።
ጉባዔውን የከፈቱትየኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) የመልማት የመበልፀግና የማደግ ተስፋ ከፊቷ የሚጠብቃት አፍሪካ ያሉባት የሰላምና ደህንነት ችግሮች ልትፈታ፣ አስተማማኝ ደህንነትም ልታሰፍን ይጠበቅባታል ብለዋል።
ሽብርተኝነትና የተደራጁ ወንጀሎችና ፅንፈኛ እንቅስቃሴዎች ፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ፣ የሳይበር ጥቃት እንዲሁም የተደራጁ ወንጀሎች አሁናዊ የአፍሪካ ፈተናዎች ናቸውም ብለዋል ሚኒስትሯ።
እነዚሁ የሰላምና ደህንነት ፈተናዎችም ከመቼውም ጊዜ በባሰ ውስብስብና ተለዋዋጭ ሆነዋልም ነው ያሉት ኢ/ር አይሻ ።
በዚህ ረገድ አፍሪካዊያን ሀገራት በፀጥታና ደህንነት አጠባበቅ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ረገድም በጋራ ተቀናጅተው ሊሰሩ ፣ ልምድ ተሞክሮዎቻቸውን ሊጋሩ ይገባል ሲሊ ጥሪ አቅርበዋል።
በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የፖለቲካ ጉዳዮችና የሽብር መከላከል ዘርፍ ኃላፊው ባባቱንዴ አባዮሚ ታይዎ አፍሪካዊያን የየሀገሮቻቸውን የሰላምና ፀጥታ የማስጠበቅ ጥረት ያክል ለጋራና አህጉር ተሻጋሪ የደህንነት ፈተናዎች ትኩረት ሊሰጡ ይገባልም ብለዋል።
ፈታኝና ተለዋዋጭ የፀጥታ ችግሮች አሉባት ያሉት ባባቱንዴ በሶማሊያ ፣ በኮንጎ እንዲሁም በሳህል ቀጠና ያሉ የደህንነት ችግሮች አህጉራዊ መፍትሄና የጋራ ትብብር የሚያስፈልጋቸው ናቸውም ብለዋል።
በአፍሪካ ቀዳሚ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ድርሻ ያላት አኢትዮጵያ አህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ለምታደርገው ጥረትም በአፍሪካ ህብረት ስም ምስጋና አቅርበዋል።
ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ሀገራት ስለ ሰላም ሲባል ለከፈሉት እየከፈሉ ላሉት ውድ ዋጋ ክብር አለንም ብለዋል ።
ከጥቅምት 5 እስከ 7 በሚዘልቀው የመከላከያ ሚኒስትሮቹ ኮንፈረንስ ፓናል ውይይትና ጉብኝቶች ይካሄዳል
በአቡ ቻሌ