“የኢሬቻን ትውፊት ወደ ቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ትውልዱን ማስተማር ያስፈልጋል”

የፊንፊኔ ቱለማ አባ ገዳ ሰብሳቢ አባ ገዳ ሰቦቃ ለታ

ኦሮሞ የዳበረና የበለፀገ ባህል፣ እሴትና ታሪክ ያለው ህዝብ ነው፡፡ ይህ ህዝብ ካለው አኩሪና ቀደምት ባህሎች ውስጥ አንዱ ኢሬቻ ነው፡፡ኢሬቻ በውስጡ የያዛቸው እሴቶች፣ ክንውኖች ምንድ ናቸው? በኢሬቻ ያለው የሰላም እሴት እንዴት ይገለፃል? እሴቶችን ከማጠንከር አንጻር ከአሁኑ ትውልድ ምን ይጠበቃል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከፊንፊኔ ቱለማ አባ ገዳ ሰብሳቢ አባ ገዳ ሰቦቃ ለታ ጋር ቃለ ምልልስ  አድርገናል፤ መልካም ንባብ!

የፊንፊኔ ቱለማ አባ ገዳ ሰብሳቢ አባ ገዳ ሰቦቃ ለታ

አዲስ ልሳን፡- ስለኢሬቻ ምንነት የተወሰነ ማብራሪያ ቢሰጡን?

አባ ገዳ ሰቦቃ፡– ኢሬቻ የደስታ መግለጫ ነው፡፡ አምላክን መለመን ነው። ተራራዎች ክቡር ናቸው፤ ወንዞች ክቡር ናቸው፤ አባት ክቡር ነው፤ እናት ክቡር ናት የሚል ነው። እነዚህ ሰዎች ከጥንት ከጠዋቱ የመጡ እና መከበር የሚገባቸው ናቸው፡፡ እናት ልጇን ዘጠኝ ወር በሆዷ አርግዛ፣ አቅፋና አዝላ  በእግሩ እንዲራመድ ታደርጋለችና በልጆቿ ትከበራለች፡፡ የሌላ እናት ብትሆንም የወለደች ከሆነች በሁሉም ዘንድ አክብሮት ይሰጣታል። አባትም እንዲሁ ክብር ይሰጠዋል፤ ኢሬቻ እነዚህን ነገሮች ሁሉ የያዘ ነው፡፡

ኢሬቻ እንኳን ከዘመን ወደ ዘመን አሸጋገርከን! ለመጪው ዓመት ደግሞ የዘራሁትን አብቅልልኝ፤ የወለድኩትን አሳድግልኝ፤ ሰላምና ፍቅር ስጠኝ፤ ከሰዎች ጋር አስማማኝ፤ ጤና ስጠኝ በማለት የሰላም፣ የፍቅር፣ የመዋደድ ጥያቄና ልመና የሚቀርብበት በዓል ነው፡፡ በክረምት ወንዞች ይሞላሉ፡፡ ድፍርሱና የሞላው ውሃ ሰውንም እንስሳትንም ያገኘውን ሁሉ ጠራርጎ ይዞ ይሄዳል፡፡ በወንዞች መሙላት ምክንያት ልጆች ወደ እናትና አባታቸው ቤት አይሄዱም፤ ከወንዝ ወዲያ ሰው ቢሞት ሃዘናቸውን እንዲሁም ሰርግ ቢኖር ደስታቸውን በጋራ ተገናኝተው አይጋሩም። ወንዞች በክረምት ሞልተው ሲፈስሱ ቆይተው ጊዜያቸውን ጠብቀው ይጎድላሉ፤ አበባዎች ይፈካሉ፤ ድፍርሱ ውሃ ወደ ንፁህ እና ወደሚጠጣ ስለሚቀየር፣ የሰዎች የለቅሶ መድረሻ፣ በሰርግ በጋራ መደሰቻ፣ የአባትና እናት መገናኛ፣ የዘመድ አዝማድ መጠያየቂያ ስለሆነ ለዚህ ‘እንኳን አደረስከን’ ብሎ ምስጋና ማቅረብ ነው፤ ኢሬቻ፡፡ ለዚህም  ነው የኦሮሞ አባቶች “ለዚህ ያደረስከን አንተ ነህ” በማለት እርጥብ ሳር ነጭተው መልካ ላይ እንደ ፀበል ግራና ቀኝ የሚረጩት፡፡

ኢሬቻ ፆታ፣ ብሔር አይለይም፡፡ “ለሃገሬ ሰላም ስጥልኝ፣ ለሰዎቹ ሰላም ስጥልኝ፤ ለእንስሳት፣ ለወፎች ሁሉ ሰላም ስጥልኝ፤ ፍቅር ስጥልኝ፤ ለፍቼ ደክሜ ያረስኩትና ያበቀልኩት ሰብል ፍሬ እንዲያፈራ አድርግልኝ…” ተብሎ ይለምናል፡፡

አዲስ ልሳን፡- በዓመት ሁለት ጊዜ በሚከበሩት የኢሬቻ በዓላት ላይ ያለው አንድነት እና ልዩነት ምንድን ነው?

አባ ገዳ ሰቦቃ፡- ሁለቱ የኢሬቻ በዓላት ልመናና ምስጋና የሚካሄድባቸው እንዲሁም ከፈጣሪ ጋር ግንኙነት የሚፈጠርባቸው ናቸው። መስከረም ላይ የሚከበረው ኢሬቻ መልካ ነው የሚባለው፡፡ ከክረምቱ ማለፍ ጋር ተያይዞ ወንዙ ጎድሎ ሰዎች የሚቀራረቡበት፣ የታረሰ እርሻ ፍሬ እንዲያፈራ የሚለመንበት ነው፡፡ የሚከበረውም ወንዝ ዳር ነው፡፡

ኢሬቻ ቱሉ ከመሬት ከፍ ባለ ተራራ ላይ ተወጥቶ የሚከበር ነው፡፡ ይህ በዓል ፈጣሪ የሚለመንበት ነው፡፡ ልመናችን ወደ ፈጣሪ እንዲደርስ አለመግባባት ውስጥ የነበሩ ሰዎች ከልጆቻቸው፣ ከሚስቶቻቸው፣ ከጎረቤቶቻቸው እንዲሁም በየቀበሌው እርቅ ይፈፀማል፡፡ እጅ ለእጅ ይያያዛሉ፣ ይሳሳማሉ፤ ቂማቸውን ይቅር ይባባላሉ፡፡ ቂም ተይዞ ወደ ልመና አይኬድም። ምክንያቱም ኢሬቻ የፍቅርና የአንድነት መገለጫም ነው።  ጦርነትን ከሃገራችን ላይ አርቅልን፤ የተቆጣውን አብርድልን፣ የወጣውን ወደ ቤቱ መልስልን፣ ወደ ሰላም አምጣልን፣ ያኮረፈውን አስታርቅልን… እየተባለ የሚለመንበት ነው፡፡

አዲስ ልሳን፡-  አባ ገዳዎች እርጥብ ሳር ይዘው የሚያቀርቡት ምስጋና አንድምታው ምንድን ነው?

አባ ገዳ ሰቦቃ፡– በወርሃ መስከረም ኢሬቻ የሚከናወነው በወንዝ ዳር ሲሆን ለፈጣሪ ምስጋና ይቀርባል፡፡ “ህዝባችንን ሰላም አድርግልን፤ ብሔሮችና ብሔረሰቦችን ሰላም አድርግልን፤ ሃገራችንን ወደ ጥሩ የእድገት ደረጃ ከፍ አድርግልን” እየተባለ በሳሩ ውሃ ይረጫል፤ ለሌሎች እንዲዳረስም እርስ በርስ ወጣቶች ይረጫጫሉ፡፡ ይህ የታመመው እንዲፈወስ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሰላምና የአንድነት ምልክት ነው፡፡  ለሃገር ሰላም ያለው አስተዋፅኦም የጎላ ነው፡፡

በኢሬቻ በዓል ላይ ወጣቶች የመታደማቸው ዋናው ምክንያት ወጣቶች የነገ ሃገር ተረካቢ ትውልድ በመሆናቸው ነው። ከአባቶች አርዓያነት እንዲማሩ ነው፡፡ ስርዓቱ የሁሉም ብሔር ወጣት ወጥቶ እንዲያመሰግንና ሰላምም እንዲመጣ እንዲለምን ስለሚፈቅድ ይወጣሉ፡፡

ወጣቶች ከአባቶች እና እናቶች ጋር መውጣታቸው አባቶችና እናቶች የሚያደርጉትን እንዲያዩና እንዲለምዱ ነው፡፡ በፖለቲካም፣ በልማትም፣ ፈጣሪን በመለመን የነገ ሃገር ተረካቢዎቹ የአባቶችን ፈለግ እንዲከተሉ ነው። ባህሉና ትውፊቱ ተጠብቆ እንዲቀጥልና ምስጋናውም እንዳይቋረጥ ነው፡፡

አዲስ ልሳን፡-  የኮሪደር ልማቱ የአደባባይ በዓሉ ምቹ እና የበለጠ እንዲፈካ ከማድረግ አንጻር የሚኖረውን አስተዋጽኦ እንዴት ይገልጹታል?

አባ ገዳ ሰቦቃ፡- በከተማዋ የተገነባውና እየተገነባ ያለው የኮሪደር ልማት የሃገር ልማት ነው፡፡ የሃገር እድገት ማሳያ ነው፡፡ ብዙ ችግሮችን ያቃልላል፡፡ ለእግረኛ፣ ለተሽከርካሪ እንዲሁም ለሁለት እግር ተሽከርካሪ (ሳይክል) ለየብቻው መንገድ ተሰርቷል፡፡ በተለይ እንደ መስቀልና ኢሬቻ ያሉ የአደባባይ በዓላት ሲከበሩ ሰዎች ስለሚበዙ ሰፋ ተደርጎ መሰራቱ እግረኛው ወይም ታዳሚው በእግረኛው መንገድ እንዲንቀሳቀስ፣ በሃገራችን አስከፊ የሆነውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስና ለመከላከል የሚያግዝ ነው፡፡ ከተማዋ ከሌሎች ከተሞች ጋር በውበቷና በልማቷ እንድትወዳደር ያደርጋል፡፡ የበዓሉ ታዳሚዎች የተሰሩትን መንገዶች፣ ለውበት ተብለው የተተከሉ ሳር፣ ችግኞችንና አበባዎችን ማበላሸት የለባቸውም። በጥንቃቄ መንቀሳቀስና ኢሬቻውን አክብሮ መመለስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ዘንድሮ የተተከለው ችግኝ ለሚመጣው ዓመት ጥላ ይሆናልና፡፡

አዲስ ልሳን፡-  የኢሬቻ  ባህላዊ ትውፊት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ከማን ምን ይጠበቃል?

አባ ገዳ ሰቦቃ፡- የኢሬቻን ትውፊት ወደ ቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ትውልዱን ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ አባቶችና እናቶች በየቤታቸው ልጆቻቸውን ማስተማርና መንገር አለባቸው፡፡ አባ ገዳዎችም በሚገባ ትውፊቱን ማስተማር፣ ማስረዳት በተግባርም ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ልጆች ደግሞ እናትና አባቶቻቸው፣ አባ ገዳዎች የሚሏቸውን ነገር መቀበልና ትውፊቱ ተጠብቆ እንዲቀጥል ሊያደርጉ ግድ ነው፡፡ የሃገራችንን ባህላዊ ትውፊት እንዲቀጥል መምህራንም ጭምር የግብረ ገብ ትምህርት ማስተማር አለባቸው። በቤታችን ውስጥ ሁሉም ብሄር አለ፤ እርስ በርስ የተጋመድን ነን፡፡ ከአባቶች የሚጠበቀው ያለፈውን ታሪክ ማውራት ሳይሆን ዛሬና ነገ እንዴት አብረን መኖር፣ ማደግ እንዳለብን ባህሉና ወጉን ማስተማር ነው፡፡ እናትና አባቶቻችንን እንዴት ማክበር እንዳለብን ልናስተምር ይገባል፡፡

መደበኛው ፍርድ ቤት በመረጃ ሲወስን፣ አሸናፊና ተሸናፊ ሲኖረው፤ ባህላዊ ፍርድ ቤት ግን በባህል መሰረት በቃለ መሃላ ያለምንም ወጪ ያስታርቃል፤ እርቁም ዘላቂነት ያለው ነው፡፡ አስተዳደጋችንና ባህላችን ይሄ ነው፡፡ “የእናትህ ጓደኛ ለአንተ እናትህ ናትና አክብራት፣ የአባትህ ጓደኛም ለአንተ አባትህ ነውና አክብረው፣ ታላቅህን አክብር! ተከባበሩ” በሚል ትውፊታችንን ለልጆቻችን ካስተማርን የነገ ሃገር ተረካቢ ዜጋ ይሆናሉ፡፡

አዲስ ልሳን፡- ለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን፡፡

አባ ገዳ ሰቦቃ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review