AMN – መስከረም 14/2017 ዓ.ም
የኢሬቻን የሰላምና የአንድነት እሴት ለዓለም ለማስተዋወቅ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ፡፡
ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የኦሮሞ ባህል ጥናት ተመራማሪ ጀምጀም ኡዴሳ፣ ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ አምላኩን የሚያመሰግንበት ታላቅ በዓል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ኢሬቻን ጨምሮ ሌሎች ያሏትን ሃብቶች ለሰላምና ለውይይት በመጠቀም ሀገራዊ አንድነትን ማምጣት ይገባልም ብለዋል ምሁሩ፡፡
በኦሮሞ ባህል ሴቶች ትልቅ ክብር እንዳላቸው የገለጹት በኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ እውቀት ተመራማሪና መምህር ሌንን ቁጦ፣ በኢሬቻ በዓል ላይም በደረጃ ከፊት ተሰልፈው በዓሉን እንደሚያከብሩ ገልጸዋል፡፡
በዓሉ በርካታ ድሎች እና ሀገር በቀል እውቀቶች ለገበያ እንዲቀርቡ ምቹ መደላድል የሚፈጠርበት መሆኑን የተናገሩት ተመራማሪው ጀምጀም በዓሉ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክትም ጠይቀዋል፡፡
የሰላምና የእርቅ በዓል የሆነውን የኢሬቻ በዓል እና መሰል ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን ህዝባዊ በዓላት አስፈላጊውን ትኩረት በመስጠት ፣ ማህበራዊ መስተጋብርን ማጠናከር እና ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነትን ማጎልበት እንደሚገባም ምሁራኑ ገልጸዋል፡፡
በሄለን ጀንበሬ