AMN – መስከረም 23/2017 ዓ.ም
የ2017 ዓ.ም የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በስኬት እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን ጥምር የፀጥታ ሀይሉ አስታውቋል።
ቅዳሜ መስከረም 25 ቀን 2016 ዓ/ም በአዲስ አበባ የሚከበረው የ2017 ዓ.ም የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓላዊ ትውፊቱን ጠብቆ በድምቀትና በሰላም እንዲጠናቀቅ ጥምር የፀጥታ ሀይሉ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቋል፡፡
የፀጥታ አካላቱ ለሚያከናውኗቸው ተግባራት በተዘጋጀው የማስፈፀሚያ ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄዷል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ም/ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ውይይቱን መርተውታል፡፡
በውይይቱ ላይ በዓሉ ባህላዊ ስርዓቱን ጠብቆ በስኬት እንዲከበር ለማስቻል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ በርካታ የፀጥታ ሀይል ተሰማርቶ ወደ ስራ መገባቱ ተገልጿል፡፡
የበዓሉ ገፅታ የሚያጠለሽ እና ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎችና መልዕክቶችን እንዲሁም ከበዓሉ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ቁሶችን ወደ በዓሉ ስፍራ ይዞ መምጣት ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑም በመድረኩ ላይ ተነግሯል፡፡
ክብረ በዓሉን ለእኩይ ዓላማ ለመጠቀም የሚደረጉ ማንኛውም ዓይነት ሕገ-ወጥ ተግባራት በፍፁም ተቀባይነት እንደሌላቸውና ይህንን ለማድረግ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ የተለያዩ የሸገር ከተማዎች አካባቢዎች በርካታ ህዝብ በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማዋ እንደሚገባ ታሳቢ በማድረግ መላው ህብረተሰብ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን በመቆም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥምር የፀጥታ ሐይሉ ማሳሰቡን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡