
AMN- ህዳር 4/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያና የሩሲያን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በሁለቱ ሀገራት መሪዎች የተደረሰው ስምምነት ወደ ተግባር እየተቀየረ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
ከሁለት ሳምንታት በፊት በተካሄደው 16ኛው የብሪክስ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት የሀገራቱን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር መስማማታቸው ይታወቃል፡፡
ይህን ተከትሎም የኢትዮ-ሩሲያ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በፎረሙ መክፈቻ መርኃ- ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የኢትዮጵያና የሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ረዥም ዘመን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀገራቱ በተለይም በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ያላቸውን ትብብር እያጠናከሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በቅርቡ በሩሲያ በተካሄደው 16ተኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ወቅት የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በመሪዎች የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ ፎረሙ መዘጋጀቱን አንስተዋል።
ይህም የሀገራቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተግባራዊ እርምጃ ማሳያ ነው ብለዋል።
መንግስት ያደረገው አጠቃላይ ሀገራዊ ሪፎርምም ኢትዮጵያ የሩሲያና ሌሎች ሀገራት ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲያቸውን ወደ ላቀ ትብብር ለማሸጋገር እየሰሩ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የቴክኖሎጂ ሽግግር ይበልጥ ለማጠናከር ዛሬ የተከፈተው የቢዝነስ ፎረም ጠቃሚ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታየ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የሩሲያና የሌሎች ሀገራት ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።
ይህ ፎረምም የሩሲያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በቴሌኮም፣ በአይሲቲ፣ በአውቶሞቲቭ፣ በኬሚካል ኢንዱስትሪና ሌሎችም ዘርፎች ያሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ላይ እንዲሳተፉ የሚያደርግ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የሩሲያ ፌዴሬሽን የንግድ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፓዶልኮ፣ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ይበልጥ ተቀራርበው እንዲሰሩ ያስቻለ ነው ብለዋል።
በዚህ የመጀመሪያው የቢዝነስ ፎረም 26 ትልልቅ የሩሲያ ኩባንያዎች መገኘታቸውን ገልጸዋል።
የሩሲያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑም ነው የተናገሩት።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በተካሄደው 16ኛው የብሪክስ ጉባኤ ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ባደረጉት ውይይት የሀገራቱን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማጠናከር መስማማታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡