AMN – ታኅሣሥ 10/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የማዕድንና አምራች ኢንዱስትሪው ትስስር ወሳኝ መሆኑን ሚኒስትሮች ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን በአምራች ኢንዱስትሪ ራስን የመቻል ግብ ለማሳካት የግሉ ዘርፍ ሚና ጉልህ እንደሆነም ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ሚኒስትሮች በቢሾፍቱ ከተማ የብረት ኢንዱስትሪ መንደር የሚገኘውን ስቲሊ አር ኤም አይ የብረታብረት ማምረቻ ፋብሪካን ጎብኝተዋል።
ሚኒስትሮቹ በሰጡት ማብራሪያ ፋብሪካው በብረት ተኪ ምርት ተምሳሌት የሚሆን ሥራ እያከናወነ ነው ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፥ በፖሊሲ ደረጃ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ትኩረት እንደተሰጠው አብራርተዋል።
ከፖሊሲው መውጣትና ከኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኋላ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርት የገበያ ድርሻ ወደ 40 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል።
በአንድ ዓመት ከ2 ነጥብ 84 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ከውጭ ይመጡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን አንስተዋል።
ከዚህ ቀደም ብረት ሙሉ ለሙሉ ከውጭ ይመጣ ስለነበር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እናወጣ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ ቁርጥራጭ ብረቶችን በመጠቀም ያለቀላቸው ምርቶችን በማምረት የገበያ ድርሻን ከፍ ከማድረግ በላይ ከውጭ የሚገቡትን በከፊል መተካት ተችሏል ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለብረት ፋብሪካዎች ምርትና የገበያ ድርሻ ማደግ ከፍተኛ ዕድል መፍጠሩን በማንሳት የማምረት አቅማቸው ከ20 ወደ 35 በመቶ ማደጉን አንስተዋል።
ሀገር እየገነባን ነው ያሉት የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው፥ ለዚህ አስፈላጊ ከሆኑት መካከል የብረታብረትና የሲሚንቶ ግብዓት ወሳኝ ናቸው ብለዋል።
የሲሚንቶ እጥረትን መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በቅንጅት እየቀረፉ መሆኑን በማንሳት፤ የብረታብረት ዘርፉን ዕድገት ለማፋጠን ጅምር ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ማዕድን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር መሃል ላይ የሚያስፈልግ ወሳኝ ግብዓት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ እምቅ የብረት ማዕድናትን አውጥቶ መጠቀም ላይ ወደ ኋላ ቀርተናል ብለዋል።
በዚህ የተነሳም ፋብሪካዎች በግብዓት እጥረት ምክንያት በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ቁርጥራጭ ብረቶችንና በከፊል ያለቁ ምርቶችን በማስገባት ጭምር ወደ ተሻለ ምርት ስለመግባታቸውም አንስተዋል።
አሁን ላይ የግንባታ ዘርፉ እያደገ በመሆኑ ከ2 ነጥብ 5 እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የብረት ግብዓት እንፈልጋለን ያሉት ሚኒስትሩ ይህንን ለመተካት በሀገር ውስጥ ለማምረት እየተሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ለዘላቂ ብረታብረት ኢንዱስትሪ ዕድገት የአይረን ኦር ማዕድንን በአግባቡ አውጥቶ መጠቀም ላይ ይሠራል ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)፥ ኢትዮጵያ ራሷን መቻል አለባት የሚለውን የመንግሥት አቅጣጫ የሚተገብረው የግሉ ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ የሚሳካው በአምራች ኢንዱስትሪው መጠናከር ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ከማዕድን ጋር የተሣሠረ የአምራች ዘርፍን መገንባት ለሀገር ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በዚህም የሀገር ፍላጎት ከመሸፈን አልፈን ለቀጣናው መላክ የሚያስችል አቅም እንደምንፈጥር የስቲሊ አር ኤም አይ ፋብሪካ ማሳያ ነው ብለዋል።
የስቲሊ አር ኤም አይ የብረታብረት ማምረቻ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተፈራ ለማ፥ ፋብሪካው በዓመት 620 ሺህ ሜትሪክ ቶን ብረት የማምረት አቅም እንዳለው ጠቅሰዋል።
ቁርጥራጭ ብረቶችን በማቅለጥና እሴት ጨምሮ ተኪ ምርት በማምረት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ በማዳን ለሀገር ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።