AMN- ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ከየዩ ኤን ኤፍ ፒ (UNFPA) ሪጅናል ዳይሬክተር ሊዲያ ዚጎሞ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከዩኤን ኤፍ ፒ ኤ የምስራቅና ምዕራብ አፍሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር ሊዲያ ዚጎሞ ጋር በዘርፉ በትብብር በሚሰሩ ተግባራት ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ላይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት በማረጋገጥና ሴቶችን በማብቃት በሁሉም ዘርፎች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየሰራ መሆን ገልፀዋል።
ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃትንና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ከመከላከል፣ ምላሽ ከመስጠትና ሴቶችን ከማብቃት አኳያ የሚስተዋሉትን ተግዳሮቶች ለመፍታት የሚያስችል የፖሊሲ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
የተባበሩት መንግስታት የስህዝብ ልማት ፈንድ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው እያደረገ ላለው ድጋፍም ሚኒስትሯ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን፣ ያለዕድሜ ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን መከላከልና አፍላ ወጣቶች ላይ ያተኮሩ ተግባራትን በቅንጅት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል።
የዩኤን ኤፍ ፒ ኤ የምስራቅና ምዕራብ አፍሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር ሊዲያ ዚጎሞ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስት ያለዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል በወሰደው እርምጃ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱን በማስታወስ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የ10 ዓመት የልማት እቅድ እና ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር በማስተሳሰር በተጠቀሱት ዘርፎች ላይ ያተኮረ የአምስት ዓመት የሪጅናል ፕሮግራም እየተዘጋጀ መሆኑን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
አጋርነት የበለጠ በማጠናከርና ለአቅም ግንባታ ተግባራት ትኩረት በመስጠት በዘርፉ የተቀመጡ እቅዶችን ወደ ተግባር ለማሸጋገር በጋራ እንደሚሰሩ የተቋማቱ ኃላፊዎች ማስታወቃቸውን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።