AMN – ጥቅምት 4/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የፍትሕ፣ የአንድነት፣ የእኩልነትና የአርበኝነት ኅብረብሔራዊ መገለጫ ምልክት ነው ሲሉ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
17ኛው የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየተከበረ ነው፡፡
በዚሁ ጊዜ አቶ አደም ፋራህ እንዳሉት፥ ሰንደቅ ዓላማ ወሳኝ ሀገራዊ የሉዓላዊነት አሰባሳቢ ምልክት ነው ።
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማም የፍትሕ፣ የአንድነት፣ የእኩልነትና ለሀገር ሉዓላዊነት የሚከፈል የአርበኝነትና የኅብረብሔራዊ አንድነት መገለጫ ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።
ለሠንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብር መስጠት ማለትም የሀገርን ሉዓላዊ አንድነት ለማስጠበቅ ውድ ዋጋ ለከፈሉና ለሚከፍሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት እንዲሁም ቀደምት ጀግኖች አርበኞችን ማክበር እንደሆነም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚተጉ ብርቱ ክንዶችን ማክበርም ሌላኛው የሀገር ምልክት የሆነውን ሠንደቅ ዓላማ ማክበር እንደሆነ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በሌላ መልኩም ለሀገራቸው ሉዓላዊ ምልክት ክብር መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን በማሰብ ለኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የተከፈለውን ውድ ዋጋ በማስተማር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።